ታህሳስ ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-16 የ አውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በፃፉት ግልጽ ደብዳቤ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን እንዲፈታ ጥያቄ አቀረቡ።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የ አረብ አለም አብዮት በ ኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ሰፊ ስለመሆኑ በድረ ገጾች በመጻፉ ሳቢያ የስብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት የ 18 ዓመት እስራት እንደተወሰነበት የጠቀሱት የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላቱ፤ ይህም አልበቃ ብሎ ባለቤቱና ልጁ የሚጠቀሙበት ንብረት ይወረስ ዘንድ በ ዐቃቤ ህግ ጥያቄ ቀርቦ ጉዳዩ ለውሳኔ በቀጠሮ ላይ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የማክበር ግዴታ እንዳለባት የሚያሣስበው የፓርላ አባላቱ ደብዳቤ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ያገኙትን ልዩ የ አገር መምራት ዕድል በተለይ የሰብዓዊ መብት አያያዝን አስመልክቶ ኢትዮጵያን ወደፊት በማራመዱ በኩል ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሚፈታበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል።
<<በ ዓለማቀፍ ደረጃ የተረጋገጠው ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በ ኢትዮጵያ መንግስትም ሊከበር ይገባዋል የሚለው ነጥብ በ አውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላቱ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል>>ብለዋል፦የፍሪደም ናው ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ማራን ተርነር።
<< ሀሳቡን በመግለጹ ምክንያት በሚገርም ሁኔታ በኢትዮጵያ መንግስት የታሰረው እስክንድር ሊፈታ ይገባል>>ሲሉም አክለዋል-ተርነር።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በ አስቸኳይ እንዲፈታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደብዳቤ የፃፉት 16ቱ የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት፦ የተከበሩ አሌክሳንደር ግራፍ ላምብስዶርፍ፣ የተከበሩ አና ጎሜዝ፣ የተከበሩ ቻርለስ ታኖክ፣የተከበሩ ኤድዋርድ ኩካን፣ የተከበሩ ኢጃ ሪታ ኮርሆላ፣የተከበሩ ኤሚሎ መነንደዝ ዴል ቫሊ፣የተከበሩ ፊዮና ሀል፣የተከበሩ ፍራንክ እንጄል፣ የተከበሩ ኪንጋ ጋል፣የተከበሩ ላይማ ሊውሺያ አንድሪከን፣የተከበሩ ማሪያዳ ግራሻ ጉርቫልሆ፣የተከበሩ ማሪካ ጋብሬል፣የተከበሩ ማይክል ጋህለር፣የተከበሩ ኖርበርት ኒውሰር፣የተከበሩ ኦሌ ሰቺሚድት እና የተከበሩ ዳቪድ ማርቲን ናቸው።