የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና መታሰር ዙሪያ ለኢትዮጵያ መንግስት ቀጥታ ደብዳቤ ጻፈ። የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ በአዲስ አበባ የሚደረገው መጪው የህብረቱ ስብሰባ አሣስቦኛል አለ

ታኅሣሥ ፯ (ሰባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ  ለኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታ በጻፈው ኦፌሴላዊ ደብዳቤ የኢትዮጵያ መንግስት  የተቃዋሚ ፓርቲ መሪውን ፕሮፌሰር መረራን ያሰረበትን ምክንያት በዝርዝር እንዲገልጽለት ጠይቋል።

የህብረቱ  ፓርላማ ፕሬዚዳንት ማርቲን ስቹልዝ ለኢትዮፕያው ፕሬዚዳንት ለዶክተር ሙላቱ ተሾመ በጻፉት ደብዳቤ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረሱ መሪ የፕሮፌሰር መረራ መታሰር እንደረበሻቸው ገልጸውላቸዋል። በመሆኑም በፕሮፌሰር መረራ ላይ የተመሰረተውን ክስ  በግልጽ እንዲያሳውቋቸው ጠይቀዋል።

የህብረቱ ፓርላማ  ፕሬዚዳንት በዚሁ ደብዳቤያቸው ፕሮፌሰር መረራ  ባለፈው ህዳር ወር   ከብራሰልስ  ካደረጉት አጭር ቆይታ መልስ መታሰራቸውን በመጥቀስ፣ በጉብኝታቸው ከአውሮፓ ህብረት  ፓርላማ አባላት ጋር ተገናኝተው እንደነበር አውስተዋል። በብራሰልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፕሮፌሰር መረራ የታሰሩት በአዲስ አበባው መንግስት ሽብርተኛ ብለው ከተፈረጁ  ሰዎች ጋር በመገናኘታቸው መሆኑን እንደገለጹላቸው በደብዳቤያቸው የጠቀሱት ማርቲን ስቹልዝ፤ እስራቸው  በህብረቱ ፓርላማ ከተደረገው ስብሰባ ጋር የተገናኘ  መሆኑንም አክለዋል።

ለዶክተር ሙላቱ በጻፉት በዚሁ ደብዳቤ “  የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ  ከውጪ መንግስታትም ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለያዩ ድምጾች የሚሰሙበት የዲሞክራሲ ተቋም መሆኑን ላስታውስዎት እወዳለሁ”ብለዋል ማርቲን ስቹልዝ። ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና  ባለፈው ወር በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት  ከሪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ከአትሌት ፈይሳ ሌሊሳና ከፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ጋር  ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገው ሲመለሱ ከቦሌ አውሪፕላን ማረፊያ በደህንነቶች ታፍነው መታሰራቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የደነገገችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  የፊታችን ጥር ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የህብረቱ ስብሰባ ላይ ችግር እንደሚፈጥርበት የአፍሪካ ህብረት ገልጿል። እንደ አፍሪካን ኒውስ ዘገባ ስጋቱንና ቅሬታውን ያንጸባረቁት ፤ የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር  ዶክተር ንኮሳዛና  ድላሚኒ ዙማ  በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትን ዶክተር ወርቅነህ ገበዬሁን  ማክሰኞ ዕለት በህብረቱ ዋና ጽህፈት ቤት ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው። በዚሁ ጊዜ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ በሀገሪቱ ያለው ውጥረት መብረዱንና  ስብሰባውን የሚያውክ ምንም ዓይነት መሰናክል ሊፈጠር እንደማይችል ለህብረቱ ሊቀ መንበር ማረጋገጫ መስጠታቸው ታውቋል።

ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ውይይጥ መንግስት ለችግሩ መንስኤና መባባስ የሆኑትን እንደ ወጣት ሥራ አጥነት ያሉትን  ችግሮች በመፍታት ችግሩን  ለማስወገድ  ከህዝቡ ጋር ሙሉ በሙሉ ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውም በህበረቱ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት መካከል ያለው ግትንኙነት እንደወትሮው ጠንካራ ሆኖ እንደሚዘልቅና   አዲስ አበባም በህብረቱ መዲናነት ቦታዋ እንደምትቀጥል እምነታቸው እንደሆነ ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል። በህዝባዊ አመጽ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብት ኩባንያዎች መቃጠላቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጓን ያወሳል የአፍሪካ ህብረት ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተነሳው ተቃውሞ ከ500 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ  ጠቅሷል።