ጥር ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 7ቱ ዋና ዋና የአውሮፓ ህብረት የፖለቲካ ድርጅቶች ኢትዮጵያን በተመለከተ የቀረበውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አጽድቀዋል። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የቀኝ አክራሪዎች ብቻ ውሳኔውን ተቃውመውታል። ለህጉ መጽደቅ ከፍተኛ ትግል ሲያካሂዱ የሰነበቱት የህብረቱ የፓርላማ አባል ሚስ አና ጎሜዝ በውሳኔው መደሰታቸውን ተናግረዋል። “በጣም ጠቃሚ የሆነ ሰነድ ነው፣ በተለይ ዋና ዋና የሚባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የውሳኔው ሰነድ ሳይለወጥ እንዲቀጥል ማድረጋቸው ትልቅ ነገር ነው” ሲሉ አክለዋል።
የተላለፈው ውሳኔ ምን ያክል ጠንካራ ነው የተባሉት አና ጎሜዝ፣ በኦሮሞ እና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ ያወግዛል፣ እስክንድር ነጋን የመሰሉ ጋዜጠኞች፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች ፖለቲከኞችም እንዲፈቱ ይጠይቀዋል ብለዋል። ባለፉት 10 አመታት በኢትዮጵያ ላይ ከተላለፉት ውሳኔዎች ውስጥ የአሁኑ ጠንካራ መሆኑን የገለጹት ሚስ አና ጎሜዝ በተለይ ዋና ዋና የሚባሉት 7ቱ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳለ መቀበላቸው ትልቅ ውጤት ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የህብረቱ ባለስልጣናትንና አዲስ አበባ የሚገኙ የህብረቱን ተወካዮች ለማግባባት ቢሞክርም፣ የህብረቱ የፓርላማ አባላት ግን አንቀበልም በማለት ማጽደቃቸውን አክለዋል
ከዚህ በሁዋላ የአውሮፓ መንግስታት ፣ በ7ቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደገፈውን የፓርላማ አባላቱን ውሳኔ ሊያጣጥሉት አይተው እንዳላዩ ሊያልፉት አይችሉም” ያሉት አና ጎሜዝ ፣ ይህን ካደረጉ በራሳቸው የፖለቲካ ህይወት ላይ ተጽእኖ እንደሚያመጣባቸው አስረድተዋል
ህብረቱ በቅርቡ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸሙትን ግድያና የሰብአዊ መብት ጥሰት በጽኑ አውግዟል። የ140 ሰዎች ግልጽ፣ ተአማኒ እና ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲመረመር ጠይቋል። ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በነጻ እንዲንቀሳቀሱ ሁኔታዎች እንዲመቻቹም አሳስቧል።ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን እንዳያባብሰው፣ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ብሎአል።
በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኤክስፐርቶች የጸጥታ ሃይሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚወስዱትን እርምጃ እንዲያቆም ጠይቀዋል። “የተገደለውና የታሰረው ህዝብ ቁጥር መንግስት ህዝቡን እንደ አጋር ሳይሆን እንደእንቅፋት እንደሚያየው” የሚያመለክተው ነው ያሉት ኤስፐርቶች፣ ምንም እንኳ መንግስት እቅዱን መተውን ቢናገርም ግድያው ፣ ማሰሩና ከልክ በላይ ሃይል መጠቀሙ አሁንም አሳስቦናል ብለዋል።
የታሰሩት በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንዲሁም ድርጊቱን የፈጸሙት የጸጥታ ሃይሎች በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።