የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን መንግስት ለማውገዝ በተዘጋጀው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል

ጥር ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህብረቱ አባላት አዘጋጅተው ባቀረቡት ሰነድ ላይ ህብረቱ ነገ ሃሙስ 11 ሰዓት ላይ ድምጽ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ለህብረቱ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ የኢህአዴግ መንግስት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የወሰደውን ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እንዲሁም በመላ አገሪቱ የሚፈጽመውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ያወግዛል። በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲካኞችና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲፈቱ ይጠይቃል። ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠው እርዳታ በቅድመ ሁኔታ ላይ እንዲቀመጥም ያሳስባል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ራፖርተር በኦጋዴንና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ወደ አገሪቱ ገብቶ እንዲያጣራ ከመንግስት ፈቃድ እንዲያገኝ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተጠቅሷል።
ጠንካራ የተባለውን ውሳኔ ሃሳብ ለማሳለፍ ዛሬ በተለያዩ የፓርላማ አባላት መካከል ክርክር ተካሂዷል። የውሳኔ ሃሳቡ ሳይቀየር እንዳለ ከተላለፈ፣ በአውሮፓ ህብረትና በኢትዮጵያ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተጽኖ ይፈጥራል። የኢህአዴግ መንግስት የውሳኔ ሃሳቡ እንዳይጸድቅ በደጋፊዎቹ በኩል ከፍተኛ የዲፐሎማሲ ስራ እየሰራ ነው።
የህብረቱ አባላት በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ጠርተው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር፡፡ የአርበኞች ግንቦት7 ሊ/መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋም ከወራት በፊት ከተለያዩ የህብረቱ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ስለኢትዮጵያ ውቅታዊ ሁኔታ ገለጻ ማድረጋቸው ይታወሳል።