የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ስላለው የዴሞክራሲ ችግር ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እየተወያየሁ ነው አለ

ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዴሞክራሲ ችግሮች ላይ ዝምታን መርጧል የሚል ትችል እየቀረበበት ያለው የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ ያለውን ችግር በተለያዩ መድረኮችና ከባለስልጣናት ጭምር በመግለጽ ላይ መሆኑን አስታወቀ።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉና ከጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩት የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት “ትክክለኛ የሆነ አመራር በአፈና ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም” ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል ቅሬታቸውን መግለጻቸውንም ይፋ አድርገዋል።

በአውሮፓ ፓርላማ ካሉ የፖለቲካ ተወካዮች መካከል ዋነኛ የሆነው የሶሻሊስትና የዴሞክራቲክ ጥምር ፕሬዚደንት የሆኑት ጅያኔ ቲፔላ ህብረቱ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ ዝምታን አለመምረጡና ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እየተከታተለው እንደሆነ አዲስ ስታንዳርድ ከተሰኘ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

እንደሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ሁሉ በኢትዮጵያ ያለውም የልማት እንቅስቃሴ ከዴሞክራሲ ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ አለመሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት ሽብርተናነትን ለመዋጋት በሚል በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ችላ ብሎታል ተብሎ ስለሚቀርቡ ቅሬታዎች የተጠየቁት ጂያኒ ቲፔላ በሃገሪቱ በመገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ አመራሮች ላይ የተወሰዱ የእስር ድርጊቶችን በአደባባይ በማውገዝና ስጋታቸውን በመገለጽ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በተወያዩ ጊዜ ይሁንኑ ጉዳይ በአግባቡ ማስረዳታቸውንና ህብረቱ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ይልቅ ለዴሞራሲ መከበር ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ፓርላማ ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ሊወሰዱ ስለሚገቡ ጉዳዮች የተጠየቁት የፓርላማ አባሉ፣ ህብረቱ ውሳኔውን ካስተላለፉ በኋላ የሚወሰዱ ለውጦችንንና እርምጃዎችን እየተከታተለ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን ግድያና የጅምላ እስራት ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ጉባኤን በመጥራት የተለያዩ ውሳኔዎችን ማፅደቁ ይታወሳል።

በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎች ድርጊት እንዲጣራ ጥያቄን ሲያቀርብ የቆየው ህብረቱ ከተቃውሞው ጋር በተገናኘ ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ አመራሮችና ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁም በማሳሰብ ላይ ነው።