ኢሳት (ጥር 13 ፥ 2008)
ሃሙስ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ድርጊት ያወገዘው የአውሮፓ ህብረት 15 ነጥቦችን ያካተተ የውሳኔ ሃሳብ በማጽደቅ የአውሮፓ ህብረት እርምጃን እንዲወስድ መጠየቁ ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ቀጣይ ድጋፍም የሰብዓዊ መብት መከበሮችን እየመረመረ እንዲሆን የፓርላማ ቡድኑ አሳስቧል።
የአውሮፓ ፓርላማ ያጸደቃቸው የውሳኔ ሃሳቦችም በቀጣይ ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለዚሁ እርምጃ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።
ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች የፓርላማ ቡድኑ ያጸደቃቸው የውሳኔ ሃሳቦች ለኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ መልዕክትን ያዘለ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይኸው የውሳኔ ሃሳብ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለውን የሃይል እርምጃ በማቆም የሰዎችን የመናገርና የመደራጀት መብት ኣንዲያከብር ኣሳስቧል።
መብታቸውን ተጠቅመው አደባባይ በመውጣታቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ሰዎችንም በአስቸኳይ ለእስር የተዳረጉ ሲሉ የፓርላማ አባላቱ በውሳኔያቸው ጠይቀዋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የአውሮፓ ህብረት ዝምታውን በመስበር በኢትዮጵያ መንግስት ላይ አቋሙን ይፋ እንዲያደርግ ዘመቻ መክፈታቸው ይታወሳል።