የአውሮፓ ህብረት ስደተኞች ለማስቆም 70 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ መደበ

ኢሳት (ግንቦት 30 ፥ 2008)

የአውሮፓ ህብረት የስደተኞችን ፍሰት ለመቅረፍ የሚያስችል የ70 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ እቅድ መንደፉንና በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ሃላፊዎች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዘጠኝ የመካከለኛና የምስራቅና አፍሪካ አገራት ጋር ትብብር በመፍጠር የስደተኞችን ፍሰት ለመቀነስ እንደሚሰሩ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። ይህንን እቅድ ለማስፈጸም እስከ 70 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ የሚችል የፕሮጄክት በጀት እንደተመደበ የአውሮፓ የስደተኞች ኮሚሽነር ዲሚጥሪስ አብራምፓውሎስ ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸው ተመልክቷል።

ይህም እቅድ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወቀሱትን ኢትዮጵያን፣ ኤርትራንና፣ ሱዳንን እንደሚጨምርና፣ እቅዱ በእነዚህ አገራት ጸጥታን የተመለከቱ እርዳታና ስልጠናዎች ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

የድንበር ጠባቂዎች ለማሰልጠን እና የስደተኛ ማጎሪያ ካምፖችን ለመገንባት በቂ ገንዘብ እንዲመደብ በአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መካከል ስምምነት መደረሱን ባለፈው ዜናችን መዘገባችን ይታወሳል። ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሊያና፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚጎርፉ ስደተኞችን ለመቆጣጠር የስደተኞች ማጎሪያ ካምፕ ግንባታ በሱዳን እንዲከናወን ስምምነት ላይ መደረሱን ተነግሯል። በተጨማሪም  የስደተኞችን ለመቆጣጠር በተለያዩ ቦታዎች ካሜራ እንዲተከል፣ ሌሎች የስለላ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች በተለይም በሱዳን እንዲተከሉ የአውሮፓ ህብረት ሃላፊዎች መስማማታቸውም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ቆይቷል።

ሆኖም የአፍሪካ ስደተኞችን ለማስቆም የቀረበው ይህ እቅድ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጠባቂ ድርጅቶች ተቃውሞ ገጥሞታል። በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደሉና ያስገደሉ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ለህዝቦች እንቅስቃሴና ዝውውር ቁጥጥር እንዲያደርጉ በአውሮፓ ህብረት መታጨታቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በጥብቅ ኮንነዋል። በጀርመን እርዳታ ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ኤክስፐርት የሆኑት ማሪና ፒተር በአካባቢው የጸጥታ ስጋት የሆኑና መቶ ሺዎችን ያፈናቀሉ አገዛዞች አሁን አካባቢውን እንዲያረጋጉ በአውሮፓ ህብረት መታጨታቸው እንዳስገረማቸው ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ኡመር ሃሰን አልበሽርን ጨምሮ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በህዝቦቻቸው ላይ በፈጸሟቸው ወንጀሎች ተጠያቂ መሆናቸውን የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች መክሰሳቸው በተለያዩ ጊዜ ያወጧቸው ሪፖርቶች ያስረዳሉ። ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በሱዳን ዳርፉር ግዛት የራሱን ዜጎች ያላከበረ የሱዳን መንግስት የሌላ አገር ስደተኞችን ያከብራል ብሎ እንደማያስብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።