የአውሮፓ ህብረት ልዑካን የኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ ለምክክር ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ

ኢሳት ዜና (መስከረም 12 ፣ 2008)

ከኢትዮጵያ የሚደረገውን ከፍተኛ የወጣቶች ስደት ተከትሎ የአውሮፓ ህበረት ልዩ የሉዑካን ቡድን በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ወደአዲስ አበባ መጓዙን ህብረቱ ዛሬ ረቡዕ ገለጠ።

በሃገሪቱ የሶስት ቀን ቆይታ የሚኖረው ይኸው የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ እየጨመረ በመጣው የወጣቶች ስደት እና ችግሩ በሚቀንስበት ዙሪያ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሰፊ ምክክር ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የአለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ወጣት ወደ የመንና የተለያዩ ሃገራት በመሰደድ ላይ መሆኑን ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል።

በተለይም ጦርነቱ እልባት ወደ አልተገኘባት የመን የሚደረገው ስደት አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ድርጅቶቹ፣ በየወሩ ወደ አራት ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ወደየመን በመግባት ላይ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።

እነዚሁ ከኢትዮጵያ በመሰደ ላይ ያሉ ወጣቶች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ እየተጓዙ እንደሚገኙ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ቁጥር መጨመር ተከትሎም የአውሮፓ ህብረት በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ልዩ የልዑካን ቡድን ወደ ሃገሪቱ እንዲላክ መደረጉን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የህብረቱ የልዑካን ቡድን አባላትም ከሃገሪቱ ባለስልጣናት በተጨማሪ ከተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት በችግሩ ዙሪያ እንደሚወያዩ ለመረዳት ተችሏል።

ህብረቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ተመሳሳይ ችግር ወደታየባቸው ሃገራት ልዑካንን እየላከ የሚገኝ ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ስደት የሚታይባቸው አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ሃሳቦችን ያቀርባል ተብሎም ይጠበቃል።

በጎረቤት ሱዳን በመሻገር በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ወጣቶች በስደት ላይ እንደሚገኙ ስደተኞቹን ዋቢ በማድረግ አሶሼይትድ ፕሬስ በቅርቡ መዘገቡም ይታወሳል።