የአክሰስ ሪል ስቴትና የዘመን ባንክ መስራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ታሰሩ

ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008)

የአክሰስ ሪል ስቴት እንዲሁም የዘመን ባንክ መስራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ መታሰራቸውን ከአዲስ አበባ የደረስን ዜና አመለከተ።

በመንግስት ዋስትና ወደሃገር ቤት ከተመለሱ ወራት ብቻ ያስቆጠሩት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ተመልሰው የታሰሩበት ዝርዝር ምክንያት ባይገለጽም፣ ከአክሰስ ሪል ስቴት ጋር የተያያዘ መሆኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሃይላንድ ውሃን በማምረት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ በመግባት በንግዱ አለም ታዋቂ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በየካቲት ወር 2005 ዓ ም ከመንግስት ጋር ባለመግባባት ከሃገር የወጡ ሲሆን፣ በመንግስት ተሰጣቸው በተባለ ዋስትና በየካቲት ወር 2007 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

ለሁለት ዓመታት ያክል በዱባይ ቆይተው ወደኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በነሃሴ ወር 2007 ከአክሰስ ቦርድ ሊቀመንበርነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ ሲሆን፣ በርሳቸው ምትክ ወ/ሮ መብራት ወልደትንሳዔ የተባሉ ባለአክሲዮን መሾማቸው ታውቋል።

በዋስትና ወደሃገር ቤት የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የተገባላቸውን በአደባባይ የተነገረው ቃል ታጥፎ ወደእስር ቤት የገቡበት ሁኔታ ግልጽ አልሆነም።