ሚያዝያ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመንና በበርካታ የሶሻሊስት አገሮች ሲሰራበት የነበረው የመንግስት ሰራተኛውን በአንድ ለአምስት አደራጅቶ የመቆጣጠርና የመምራት አሰራር መክሸፉን አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ተናግረዋል።
ሰሞኑን በባህር ዳር ከተማ አመራር አካዳሚ በተደረገ ስብሰባ ላይ የአካዳሚው ዳይሬክተር፣ የመንግስት ሠራተኛው የአንድ ለአምስትን ስብሰባን “መቼ ነው አላቆኝ የማየው?” በማለት በምሬት እስከ መግለጽ ደርሷል ብለዋል፡፡የዚህ ዓይነት ጥላቻ በበታች ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን በበላይ አመራሮችም ላይ መኖሩን የገለጹት ባለስልጣኑ፣ አንድ ለአምስት አደረጃጀት ያለው ጥላቻ ስር የሰደደ መሆኑን ለከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ሳይደብቁ ተናግረዋል፡፡
“በየወሩ በሚታየው የአፈጻጸም ግምገማ ላይ ጥላቻውን አይተናል” ያሉት አመራሩ ፣ አብዛኛው ቢሮዎችና ፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የአንድ ለአምስት ቃለ ጉባዔ ሲይዙ ማንም በሌለበት አንድ ሰው ጽፎ ሌሎች የሚፈርሙበት ፤ምንም ውይይት ሳይደረግ እንደተደረገ በማስመሰል ሪፖርት የሚቀርብበት እንደሆነ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
ሰራተኛው የሚሰራው አመራሩን ሲመለከት ብቻ እየሆነ መምጣቱን የገለጹ ዳይሬክተሩ፣ አመራር በሌለበት ጊዜ የትኛውንም ሥራ ለመስራት ፍላጎት እንደማያሳዩ በበርካታ ቢሮዎችና መስሪያ ቤቶች በተደረገው ግምገማ መታየቱን አብራርተዋል፡፡
ኃላፊው በከፍተኛ አመራሩ ላይ በተከታታይ የታየውን መሰረታዊ ችግር ሲያስረዱ ፣ የኮር አመራሩ በየዕለቱ በስብሰባ በመጠመዱ መደበኛ ሥራ ለመስራትና የሕብረተሰቡን እርካታ ለማግኘት አለመቻሉን ገልጸው፤ ባለጉዳይ በየቢሮው እየተጉላላ በሥራ ሰዓት ስብሰባ ማድረግ እየተለመደ በመምጣቱ ህዝቡ በአግልግሎት እጦት ይንገላታል ብለዋል።
ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት በደራሽ ስራና በመስክ ስራ ላይ በየጊዜው በመጠመዱ፣ በቢሮ የሚሰሩ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥራታቸው እየቀነሰ መጥቶ መንግስታቸው የህዝቡን ድጋፍ እያጣ የመጣበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል፡፡