የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የገዢው ፓርቲ አባላት እንዲሆኑ እየተጠየቁ ነው

መጋቢት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን በግድ የፓርቲ አባል እያደረገ ያጠመቀው ኢህአዴግ  አሁን ደግሞ በአካል ጠና ያሉትን ታዳጊ ወጣት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን የአባልነት ፎርም እያስሞላ እንደሚገኝ ምንጮች አስታወቁ፡፡

ታዳጊ ወጣቶች በጠርናፊ መምህራን በኩል እየተመለመሉ መሆኑን የገለጹት ምንጮች በዚህ ሳምንት በመላ አዲስ አበባ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩትን ታዳጊ ወጣቶች በግማሽ ቀን ሥልጠና የመግባቢያ ዝግጅት አካሂዶ እና 50 ብር የውሎ አበል ሰጥቶ በመሸንገል ፎርም እንዲሞሉ አድርጓል።

አምስት፣ አምስት የኮሚቴ አባላትም በየትምህርት ቤቱ የተመረጡ ሲሆን የኢህአዴግ ካድሬዎች መመሪያ የሚያወርዱት ለነዚህ ተማሪዎች ይሆናል ተብሎአል።

ዘጋቢያችን ‹‹ለ ተማሪ … እርስዎ የኢህአዴግ አባል መሆንዎ ይታወቃል፤ በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ መጋቢት 21 እና 22 ቀን በሚካሄደው የሙሉ ቀን ሥልጠና ላይ በ … ትምህርት ቤት ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ላይ እንዲገኙ በአክብሮት ተጋብዘዋል›› የሚል ወረቀት መመልከቱን ገልጿል።

ለሥልጠና የተመረጡት የተማሪዎች ሥም እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶችም ሥማቸው ፎርሙ ላይ በብዕር የተሞላ ሲሆን በሁለቱ ቀን ሥልጠና በቀን መቶ መቶ ብር እንደሚሰጣቸው ጠርናፊዎቻቸው በቃል እንደነገሯቸው ተማሪዎቹ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

በባህርዳር በተካሄደው 9ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ አንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ኢህአዴግ ሰዎችን ለመመልመል የሚጠቀምበት ዘዴ ከእውነተኛ ተጋዮች ይልቅ አድርባዮችን እንዲያፈራ አድርጓል በማለት እንደገና እንዲታይ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ኢህአዴግ 6 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት በተደጋጋሚ ይናገራል። በኢህአዴግ ስሌት መሰረት ከ13 ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ኢህአዴግ ነው። እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግምት ውስጥ ካስገባን ደግሞ፣ ከ5 ሰዎች መካከል አንዱ የኢህአዴግ አባል ነው ።