ኢሳት (ሰኔ 14 ፥ 2008)
በቅርቡ የገቡበት ባልታወቀው ከ5 ሺ በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቆጠር ኪሳራ እንዳጋጠመው ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከእነዚሁ ተቋማት መሬት እና ከፍተኛ ብድር በማቅረብ የስራ እድል ፈጠራን ለማስፋፋት ጥረት ቢያደርግም እቅዱ በተቃራኒው ኪሳራ መስመዝገቡ ተውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከአስር አመት በፊት ማቋቋም ለጀመረው ለዚሁ ፕሮግራም በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ የነበረ ሲሆን ሰሞኑን የከተማዋ አስተዳደር ባካሄደው ቆጠራ ከ5ሺ የሚበልጡ የገቡበት አለመታወቁ ይታወሳል።
ከአራት ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎ በተካሄደው በዚሁ ቆጠራ ወደ 4ሺ የሚገጡት የገቡበት አለመታወቁንና ወደ 1ሺ 600 የሚሆኑት ደግሞ አባሎቻቸው አለመገኘታቸውን አስተዳደሩ አስታውቋል።
የከተማዋ አስተዳደር ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሲሰጥ የቆየው መሬት ለሌላ አገልግሎት ተላልፎ የተሰጠበት አጋጣሚ መኖሩም ታውቋል።
የገቡበት ባልታወቀው በነዚሁ ድርጅቶች መንግስት በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ ያጋጠመው ሲሆን፣ የአስተዳደሩ ባለስልጣናት ጉዳዩን ለመመርመር ልዩ ቡድን ማቋቋሙን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ5ሺ በሚበልጡ ድርጅቶች ደብዛ መጥፋት የደረሰበትን ትክክለኛ ኪሳራ ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ የተመደበ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመላሽ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይፋ አድርጓል።
የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኤጀንሲ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ኢንተርፕራይዞች ባለማቅረቡ ምክንያት በጀቱ ተመላሽ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
በድርጅቶቹ ላይ የተፈጠረው ችግርና ኪሳራ መንግስት ለማቅረብ ባሰበው ብድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳደረ ሲሆን፣ የድርጅቶቹ የገቡበት አለመታወቅ የባንኩ ትርፍ እንዲቀንሱ ማድረጉን ለመረዳት ተችሏል።