የአቶ ፈቃደ ሸዋ ቀና የቀብር ስነስርዓት ቅዳሜ ግንቦት 5 ፥ 2009 ዓም አደልፊ በሚገኘው የጆርጅ ዋሽንግተን የመቃብር ቦታ እንደሚፈጸም ተገለጸ

አቶ ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2009)

የታዋቂው ምሁርና የፖለቲካ ሰው የአቶ ፈቃደ ሸዋ ቀና የቀብር ስነስርዓት ቅዳሜ ግንቦት 5 ፥ 2009 ዓም አደልፊ በሚገኘው የጆርጅ ዋሽንግተን የመቃብር ቦታ እንደሚፈጸም ተገለጸ።

የስነስርዓቱ አስተባባሪ ኮሜቴው ለኢሳት በላከው መግለጫ የአቶ ፈቃደ ሸዋቀና የቀብር ስነስርዓት የሚጀምረው በዋሽንግተን መንበረ-ፀባዖት ቅድስት ማሪያም  ቤተክርስቲያን ጠዋት ላይ በሚካሄደው ጸሎተ ፍትሃት ይሆናል።

ከጠዋቱ 9 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት AM በሚካሄደው ጸሎተ ፍትሃት ሃይማኖታዊ ትምህርትና የአቶ ፈቃደ ሸዋቀና የህይወት ታሪክ እንደሚነበብ ከወጣው መርሃ-ግብር ለመረዳት ተችሏል።

በኋላም በአደልፊ ወደ ሚገኘው የጆርጅ ዋሽንግተን ሴሜትሪ በመምራት ከቀኑ 12 ኣሽከ 1 ሰዓት PM ባለው ጊዜ የቀብር ስነስርዓቱ እንደሚፈጸም ታውቋል።

ከትናንት በስቲያ በህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት አቶ ፈቀደ ሸዋቀና፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተባረሩት 42 መመህራን አንዱ ነበሩ። ከዚያም በኋላ በስደት በሚኖሩበት አሜሪካ ሚዛናዊ በሆነ አመለካከታቸው ጉልህ የፖለቲካና የማህበራዊ ተሳትፎ የነበራቸው ሰው ናቸው።

አቶ ፈቃደ ሸዋቀና የሁለት ወንዶችና አንድ ሴት ልጅ አባት እንዲሁም የሁለት ልጆች አያት ነበሩ።