የአቶ ዘውዴ ጉደታ መታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 25/2010) የኦዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩትና በቅርቡ በድንገት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የአቶ ዘውዴ ጉደታ መታሰቢያ ፕሮግራም በዋሽንግተን ዲሲ ተካሄደ።

አስከሬናቸውም ወደ ትውልድ ሃገራቸው ኢትዮጵያ ተሸኝቷል።

የኦዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ዘውዴ ጉደታ መታሰቢያና የአስከሬን ሽኝት ትላንት በደብረሃይል ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተካሂዷል።

በዝግጅቱ ላይ የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች፣የአቶ ዘውዴ ጉደታ የስራ ባልደረቦች፣ታዋቂ ኢትዮጵያውያን፣ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አቶ ዘውዴ ጉደታ ሲሰሩበት የነበረውን የጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ በመወከል ንግግር ያደረጉት ሚስስ ቫኒ ሙርቲ አቶ ዘውዴ ስራውን የሚያከብር፣ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ተግባብቶ የሚሰራ፣ቅን አመለካከት ያለው ሰው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ በስራ ባልደረባቸው ድንገተኛ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

የኦዴግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶክተር መስፍን አብዲ በበኩላቸው አቶ ዘውዴ ጉደታ ትሁት፣ታታሪ፣ከመሆናቸው ባሻገር ሁሉንም ሰው የሚወዱና መቅረብ የሚፈልጉ መሆናቸውን አውስተዋል።

ድርጅታቸው ኦዴግ አቶ ዘውዴን በማጣቱ ከፍተኛ ሃዘን እንደተሰማው ገልጸዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመወከል ንግግር ያደረጉት ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው አቶ ዘውዴ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችንና የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማቀራረብ ድልድይ በመሆን ቀን ከሌት ሲተጉ እንደነበር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በዚህ ስራቸውም ዘወትር ሲታወሱ ይኖራሉ በማለት ገልጸዋል።

የአቶ ዘውዴ ጉደታ አስከሬን ወደ ትውልድ ሃገሩ ኢትዮጵያ የተሸኘ ሲሆን የቀብር ስነስርአታቸውም በትውልድ መንደራቸው አምቦ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እሁድ ነሐሴ 27/2010 ቀን የሚፈጸም መሆኑን ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

አቶ ዘውዴ ጉደታ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።