የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቤተሰቦች ለኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቀረቡ

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቤተሰቦች ለኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቀረቡ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ/ም) የግንቦት 7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር መፈታታቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያን ላዳረጉት ድጋፍ ቤተሰቦቻቸው ምስጋናቸውን ገልጸዋል። የአቶ አንዳርጋቸው ባለቤት ወ/ሮ የምስራች ሃይለማርያም እንዲሁም ታላቅ እህቱ ወ/ሮ ብዙአየሁ ጽጌ፣ ደስታቸውን በመግለጽ፣ ላለፉት 4 አመታት ህዝቡ ሲያደርገው ለነበረው ትግል ደስታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አርበኞች ግንቦት7 በአቶ አንዳርጋቸው መፈታት የተሰማውን ደስታ ገልጿል።
ንቅናቄው “ በጓዳችን መፈታት ደስ ብሎናል፤ የሚጠብቀን ብዙ መሆኑን እናውቃለን” በሚለው መግለጫው፣ “አቶ አንዳርጋቸው ዛሬ ተፈቶ በጉጉት ከሚጠብቀው ሕዝብና ቤተሰቦቹ ጋር ሲቀላቀል ‘ሰው እየሳቀ ለመብቱም ለሕዝቡም መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ’ ብሎ መናገሩን የጠቀሰው መግለጫው፣ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ለሁሉም የህሊና እስረኞች መፈታት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉን፣ ብዙዎች መታሰራቸውን ፣መደብደባቸውን፣ መሰደዳቸውንና ሰቆቃ የተፈጸመባቸው መሆኑን ገልጿል።
ትግሉ እሚፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ መንገድ እንደሚቀረው የገለጸው የድርጅቱ መግለጫ፣ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ኃይሎች ለዚህ ድል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን እንደሚገነዘብም አትቷል።
አርበኞች ግንቦት7 አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ ጥረት ላደረጉ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እንዲሁም ከጎናቸው ለቆሙ የውጭ አገር ዜጎችና ድርጅቶች ሁሉ ከፍተኛ ምስጋናውን አቅርቧል።
“ደስታችን የተሟላ የሚሆነው ወገኖቻችን የሞቱለት፣ የታሰሩለት፣ የተሰደዱለትና የተሰቃዩበት ዓላማ ሲሳካ ነው” ያለው መግለጫው፣ ዛሬም አቶ አበበ ካሴ፣ ሰይፉ አለሙ፣ ፍቅረማርያም አስማማው፣ ማስረሻ ሰጤ፣ መስፍን አበበ፣ አበበ ኡርጌሳ፣ ራቪድ ሳላ እና ሌሎች በርካታ ወገኖቻችን በእስር ላይ ይገኛሉ። ለእነዚህ ሁሉ ወገኖቻችን ነፃነት የምናደርገው ትግል አጠናክረን መቀጠል ግዴታችን ነው። “ ብሎአል።
“ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲ የምናደርገው ትግል ገና በጅማሮ ላይ ያለው ነው። ዛሬ በአገራችን ያየነው መልካም ጅማሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ እውነተኛ የስልጣን ባለቤት ወደሚያደርግ መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመራ ትግላችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል” ሲል አሳስቧል።
ድርጅቱ በማጠቃለያው “ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት ምክንያት ደስታችን ከፍተኛ ቢሆንም ከእንግዲህ የሚጠብቀን ትግል ከዚህ በፊት ከነበረው የበለጠ መስዋትነት ሊጠይቅ የሚችል መሆኑን በመገንዘብ ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገሩ ባለሙሉ መብት ዜጋ እስኪሆን ትግሉን መቀጠል” አለበት ሲል ጥሪ አቅርቧል።