የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታሰር የነጻነት ትግሉን አቀጣጥሎታል ሲል አርበኞች ግንቦት7 ገለጸ

ሰኔ (አሥራ  ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ንቅናቄው የድርጅቱ ከፍተኛ የአመራር አባል የታሰሩበትን ሁለተኛ አመት ለማስታወስ ባወጣው መግለጫ “ ህወሃት አንዳርጋቸው ጽጌን በእጁ ለማስገባት በአፈናው ተግባር ተባባሪ ለሆነው ለየመኑ የቀድሞ መሪ መንሱር ሃዲ መንግሥት ዘጠኝ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቢከፍልም፣ አፈናው በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ህዝባዊ ቁጣ ከመቀስቀስ እና እኔም አንዳርጋቸው ነኝ የሚሉ ታጋዮች ትግሉን እንዲቀላቀሉ እንዲሁም ወደ ተግባር ትግል እንዲገቡ ከማድረግ ውጭ በድርጅቱ ላይ ያሰበውን ድል አላገኘም ብሎአል።

“የሰነዓውን ኦፕሬሽን በህወሃት በኩል የመራውና አንዳርጋቸዉ ጽጌ እጆች ላይ ካቴና አጥልቆ ለወያኔ ያስረከበው አብረሃም መንጁስም ቢሆን በሱልጣን ሽኩቻ ከነበረበት ሃላፊነት ተፈንግሎ ዛሬ የት እንዳለ ከሱ ከራሱ ዉጭ ሌላ ሰዉ የሚያዉቅ አይመስለንም” የሚለው የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ፣ የአንዳርጋቸው መያዝ የፈጠረው ህዝባዊ ቁጣ የህወሃት መሪዎችንና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው እንደለመዱት ደረታቸውን ነፍተው በሠላም እንዳይወጡና እንዳይገቡ ወደሚያሸማቅቃቸው የተግባር እርምጃ አሸጋግሮታል ብሎአል።

ከአንዳርጋቸው መታገት በኋላ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ቁጣ የአንዳርጋቸዉ የረጅም ጊዜ ምኞትና በትግል ላይ በነበረባቸዉ አመታት በከፍተኛ ደረጃ የደከመበት የልፋቱ ዉጤት ነው ብሎ እንደሚያምን የገለጸው ድርጅቱ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ይህንን ህዝባዊ ቁጣና ህዝባዊ መነቃቃት አስተባብሮና የሚያስፈልገውን አመራር ሰጥቶ ትግሉን ከዳር ለማድረስ በሙሉ ሃይሉና ጉልበቱ እየተንቀሳቀሰ ነው ሲል አክሏል።

ንቅናቄው “የትግል ጓዳችን አንዳርጋቸው ጽጌ የታገተበትን ሁለተኛ አመት ስናስታውስ ይህ ጀግና ሰዉ የጀመረውን ትግል ከዳር ለማድረስ ያለንን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ነው” ያለ ሲሆን፣  ለፍትህ ለእኩልነትና ለነጻነት ሲታገሉ የአገዛዙ  ሠለባ የሆኑ በየዕስር ቤቱ  እየተሰቃዩ ያሉ ሁሉ ነጻ እስኪወጡ ድረስ ትግሉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በሌላ በኩል በእንግሊዝ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቀኑን በማስመልከት በእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፉ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ መሆኑን ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ ከስፍራው ዘግባለች ።