ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዓለምአቀፍ ሕግን በሚጻረር መልኩ ከየመን ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ታግተው የተወሰዱት የነፃነት ታጋዩ የአቶ አንዳርጋቸው የደኅንነት ሁኔታ እንዳሰጋው የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ የሚከታተለው ሪፕሪቭ የተባለው የህግ ባለሙያዎች ስብስብ አስታውቋል።የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት በበኩሉ የሞት ቅጣት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኘው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚገኝና የደኅንነቱ ሁኔታ ስጋት እንዳደረበት ባለፈው ሳምንት በሪፖርቱ ገልጿል።
ይህን ተከትሎ የአቶ አንዳርጋቸው ፀጌ ደኅንነት ያሰጋቸው ቤተሰቦቹ ባለፈው ቅዳሜ ለውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም፣ ካለፈው ነሃሴ ወር ወዲህ በእንግሊዝ መንግስት በኩል አለመጎብኘታቸውን ባለስልጣናቱ አሳውቀዋል። በትናንትናው እለት የእንግሊዝ የጋራ ብልጽግና አገራት የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ሚንስትር ቶቢያ ኤልውድ በጽሁፍ ለፓርላማ አባላት በላኩት መግለጫቸው እንዳሉት ካለፈው ነሃሴ ወር ወዲህ አቶ አንዳርጋቸው በእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰዎች በኩል አለመጎብኘታቸውን ገልጸዋል። እርሳቸው የጻፉት ደብዳቤ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን አቶ አንዳርጋቸው ቋሚ የሕግ ማማከር አገልግሎት እያገኙ ነው በማለት ከሰጡት መግለጫ ጋር ይጋጫል ብለዋል።
የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በአጽኖት እንደሚከታተል የእንግሊዝ መንግስት የገባውን ቃል አለማክበሩን ተከትሎ ከፍተኛ ውግዘትና ትችቶች ቀርበውበታል። ባለፈው ሰኔ ወር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርም የሕግ ከለላ ያገኛል ያሉትን እስካሁን በገቢር አለመጸማቸውን እንዳሳሰበው ሪፕሪቭ አስታውቋል። ምንም ዓይነት የህግ ከለላ ሳያገኙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ያለው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች የሞት ፍርድ ካለባት አገር ኢትዮጵያ በነጻ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የእንግሊዝ መንግስት ማንኛውንም ጥረት እና ጫና እንዲያደርግ ሲል ሪፕሪቭ ጥሪውን አቅርቧል።
በተጨማሪም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቤተሰቦች እና ልጆቹ ካለፈው ነሃሴ ወር ጀምሮ በሕይወት አለ ወይስ የለም በሚለው ጥያቄ ጭንቀት ውስጥ እንደገቡና ለህመም እንደተዳረጉ ሪፕሪቭ አስታውቋል።