የአቶ አባይ ወልዱ ባለቤት በአውስትራሊያና ኒውዚላንድ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ፥ ሌሎች የህወሃት አባላት ቁልፍ ቦታዎች ላይ እየተሾሙ ናቸው

ኢሳት (ሰኔ 14 ፥ 2008)

የትግራይ ክልል ፕሬዚደንትና የህወሃት ሊቀመንበር የአቶ አባይ ወልዱ ባለቤት በአውስትራሊያና ኒውዚላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ። ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የህወሃት አባላትና አመራሮች በአምባሳደርነት በብዛት መሾም ያስፈለገበት ምክንያት ያልታወቀ ሲሆን፣ የዋሽንግተኑንም የአምባሳደርነት ስፍራ ወደ ህወሃት ታጋይ እንደሚተላለፍ ተሰምቷል። ስፍራው ለህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ለአቶ ብርሃነ ኪዳነማሪያ እንደሚሰጥ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በቅርቡ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ብርሃኑ ከበደ የህወሃት አባል በሆኑት  በዶ/ር ሃይለሚካዔል አበራ ሲተኩ፣ በሱዳን አምባሳደር የነበሩት አቶ አሊ አብደላም ስፍራቸውን የህወሃት ታጋይ ለነበሩት አቶ አባዲ ዘሙ ለቀዋል።

በሰሜን አሜሪካ በካናዳ ኩባና ዩ ኤስ አሜርካ ብቻ ኤምባሲና ቆንስላ ጽ/ቤት ያለው የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫቸውን በአሜሪካ መዲና ዋሽንግተንና ኮሎምቢያ ጭምር አምባሳደር ሆነስ የሚያገለግሉትን አቶ ግርማ ብሩን በማንሳት የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ብርሃነ ኪዳነማሪያም ለመሾም መወሰኑን ምንጩን ገልጸዋል።

በአውሮፓ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በአሁኑ ወቅት ግማሽ ያህሉ የህወሃት ሰዎች መያዙ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በብሪታኒያ ዶ/ር ሃይለሚካዔል አበራ፣ በጣሊያን አቶ ሙሉጌታ አለምሰገድ፣ በአየርላንድ ሊላዓለም ገ/ዮሃንስ ሲጠቀሱ፣ በአውስትራሊያና ኒውዝሊላንድ ደግሞ የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባልና የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት አባይ ወልዱ ባለቤት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማሪያም በሁለቱ ሃገራት ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ተሾመዋል።

በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ካሉት ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል የሚባሉትን ሃገራት ከደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት የህወሃቱ ታጋይ አቶ አባዲ ዘሙ አቶ አሊ አብዶን ተክተው የሱዳን አምባሳደር ሲሆኑ አቶ ፍሰሃ ሻውል በደቡብ ሱዳን  ተሾመዋል።

ሶማሊያ፣ ሞቃዲሾ፣ ሰሜን ሶማሊያ ሶማሊላንድ እንዲሁም ፑንትላንድን የህወሃት ታጋዮች የነበሩና  አባላት ተሾመውባቸዋል።

ብ/ጄኔራል በርሄ ተስፋዬ በሶማሊላንድ ሃርጌሳ ሲሾሙ፣ አቶ አስመላሽ ወ/ምህረት በፑንትላንድ በካውንስል ጄኔራልነት ሚሽኑን ይመራሉ። ሊላው የህወሃት አባል አቶ ወንድሙ አሳምነው በሶማሊያ ሞቃዲሾ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ትስስር በፈጠረችው ቻይና የህወሃት መስራች አቶ ስዩም መስፍር በዋና ከተማዋ በቤጂንግ ዋና አምባሳደር ሆነ ሲቀመጡ፣ በደቡብ ቻይና ጓጁ ከተማ ካውንስልና ጄኔራል ሆነው የሚያገለግሉት ሌላው የህወሃት አባል አቶ ገ/ሚካዔል ገ/ጻድቅ ናቸው።