ሰኔ ፲፬( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ስራውን በፈቃዱ ለቋል
በአማራ ክልል ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠሉትና የህወሃት ቀኝ እጅ ተድርገው የሚቆጠሩት የአቶ ዓለምነው መኮንን የግል አጃቢ የሆነው አንዋር ሙሃመድ የተባለው ግለሰብ፣ ባህርዳርቀበሌ 04 በሚገኘው ግሪንላንድ ሆቴል ውስጥ በጥይት ተመትቶ ተገድሎ ከተገኘ በሁዋላ፣ የብአዴን ካድሬዎችና የአቶ ዓለምነው የቅርብ ወዳጆች ሽብር ውስጥ መግባታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።በመሆኑም ካድሬዎቹን ለማረጋጋት ሲባል የዞኑ የፖሊስ አዛዥ የሆነው ኮማንደር ዋኘው ግለሰቡ ራሱን እንዳጠፋ ተደርጎ እንዲነገር ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ለውስጥ አርበኞች አልተባበርም በማለቱ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ምሽት ላይ እንደተገደለ የገለጹት ምንጮች፣ በእለቱ ምሽት ላይ አቶ አለምነው መኮንን በባህርዳር እንደነበርና የግድያው ኢላማም እሱ እንደነበር ገልጸዋል። አቶ አንዋር፣ የአቶ አለምነው አካባቢ ተወላጅ ሲሆን፣ አቶ አለምነውን አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ እርምጃ እንደተወሰደበት እነዚሁ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ግድያው የተፈጸመው የብአዴን ባለስልጣናት በሚዝናኑበት ግሪንላንድ ሆቴል ነው። ከዚህ ቀደምም በዚሁ ሆቴል ግቢ ውስጥ ቦንብ መፈንዳቱ ይታወሳል።
ግድያውን ተከትሎ ትናንት በክልሉ የሚገኙ ደህንነቶች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ የክልሉ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ ስንታየሁ “ በዚህ ሁኔታ መሥራት አልችልም” በማለት ስራውን በፈቃደኝነት ለቋል። የኮማንደሩ ከኃላፊነቱ መልቀቅ ተጨማሪ ስጋት ማሳደሩን ምንጮች ገልጸዋል።
ትናንት በነበረው ግምገማ ላይ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባለሸ መሄዱ፣ በክልሉ ያለውን የትጥቅ ትግል መቆጣጠር አለመቻሉ፣ ለመረጃ ከፍተኛ ገንዘብ እየወጣ መረጃ መጥፋቱ ተነግሯል።
እንዲሁም ነገ በፖሊስ ኮሚሽን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ከመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፣ ግምገማው ወደ እርሱ ማነጣጠሩን የተረዳው ኮማንደር አሰፋ “ ዛሬ ላይ ማን ለማን እንደሚሰራ አይታወቅም” የሚልና ሌሎችንም ጠንካራ የተባሉ ትችቶችን በመሰንዘር ፣ በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን መልቀቁንና በስራው የመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል።
እንደውስጥ ምንጮች ገለጻ የብአዴን ባለስልጣናት ከህወሃት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ዙሪያ ከሁለት ተከፍለዋል።
አብዛኞቹ የክልሉ ፖሊሶችና ወታደሮች ብአዴን ራሱን ከህወሃት ተጽእኖ አላቅቆ የክልሉን ህዝብ መብትናማንነት እንዲያስከብር ይፈልጋሉ።እንዲሁም የደህንነትና የጸጥታ አባላቱ በክልሉ ከተሰማራው ኮማንድ ፖስት ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም የተደካመ ነው። ይህ ጉዳይ በፌደራል ደረጃ የተቀመጡ የህወሃት ባለስልጣናትን እያሣሰበ መምጣቱን ተከትሎ፣ በቅርቡ ሹም ሽር እንዲካሄድ ቢደረግም ነገሮች እየባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አልመጡም።