(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 4/2010) አቶ በረከት ስምኦን በደብረማርቆስ ታዩ በመባሉ በተካሄደ ተቃውሞ ቪ ኤይት ተሽከርካሪያቸው መቃጠሉ ተነገረ።
በጎዛምን ሆቴል ታይተዋል የተባሉት አቶ በረከት ስምኦን ሹፌር መታወቂያም ተገኝቷል።
በደብረማርቆስ ሕዝቡ አቶ በረከትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያደረገው ተቃውሞን ተከትሎ በአካባቢው የስልክ አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉም ታውቋል።
አቶ በረከት ስምኦን ከአምባገነኑ መሪ መለስ ዜናዊ ጋር የኢትዮጵያን መንግስት በተንኮልና በአሻጥር በመምራት የሕወሃት ተላላኪ ሆነው ላለፉት 27 አመታት ሲዘወሩ እንደነበር ይነገራል።
አሁን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ከሚቃወሙት የኢሕአዴግ ባላስልጣናት መካከል አንዱ መሆናቸውም ነው የሚታወቀው።
በቅርቡ እንደተዘገበውም በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች በመዘዋወር የጥፋት ሃይሎችን በማደራጀት አቶ በረከት ስምኦን ከሌሎች የሕወሃት ደጋፊ ከሆኑ የብአዴን ባለስልጣናት ጋር ታይተዋል ተብሏል።
እናም በዚህ መጥፎ ድርጊታቸው የሚታወቁት አቶ በረከት ስምኦን በደብረማርቆስ ከተማ ጎምዛን ሆቴል ታይተዋል መባሉን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ቁጣቸውን ገልጸዋል።
በጎዛምን ሆቴል የእሳቸው መኪና ነች የተባለች ቪ ኤይት ተሽከርካሪ መቃጠሏ ተነግሯል።
ተሽከርካሪዋ በቃጠሎ ከመውደሟ በፊት ሕዝቡ ባደረገው ፍተሻ ላፕቶፖችንና የአቶ በረከት ሹፌር ሁለት በተለያየ ስም የተዘጋጁ መታወቂያዎች ተገኝተዋል።
ሕዝቡ ቁጣውን በገለጹበት ጊዜ ከአገዛዙ ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው የሚባሉት የወይዘሮ ትልቅ ሰው ገዳሙ ሆቴል ጉዳት ደርሶበታል ተብሏል።–ጎዛምን ሆቴልም እንዲሁ
የጎዛምን ሆቴል ሕንጻን የሰሩት ሰው ለአካባቢው ልማት ሲሉ ከውጭ ሃብታቸውን ያፈሰሱ መሆናቸው ነው የተነገረው።
እናም ሕዝቡ ለራሱ ጥቅም የተገነቡ ልማቶችን ማውደሙ አግባብ አይደለም መባሉም ተነግሯል።
በደብረማርቆስ ማርሲላስ የተባለና የሕወሃት ደጋፊ የሆኑ በአንድ ግለሰብ ሆቴል ላይም ጉዳት መድረሱ ታውቋል።
በደብረማርቆስ የሕዝቡን ቁጣ ለማብረድ አድማ በታኝ ፖሊሶችና የመከላከያ አባላት ከብርሸለቆ ወደ ከተማዋ ገብተዋል።
የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በደብረማርቆስ የተፈጠረው አለመረጋጋት በአካባቢው በተላለፈ ሃሰተኛ መረጃ ምክንያት ነው በማለት ጉዳዩን ሳያብራራ አልፎታል።በደብረማርቆስ አቶ በረከት ታይተው መሰወራቸው ከተነገረ በኋላ ሌሎች ሁለት ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል ተብሏል።
አንዱ ተሽከርካሪ የዳሽን ቢራ ምርትን የጫነ እንደነበርም ተገልጿል።
በደብረማርቆስ የተኩስ ድምጽ እየተሰማ እንደሆነም ኢሳት ከአካባቢው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።