(Sept. 14) በአርማጭሆ አካባቢ በጠገዴ ወረዳ፤ ሰረቃ ከተማ፤ የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በተዘጋጀ የሐዘን መግለጫ ዝግጅት ላይ በተተኮሰ ጥይት፤ አንድ አዋቂ መገደሉንና ሌላ ወጣት ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል መግባቱ ታወቀ።
ኢሳት ከሥፍራው ያነጋገራቸው ሰው እንደገለጹት፤ ባለፈው ነሐሴ 21 ቀን በመንግሥት ባለሥልጣናት ትዕዛዝ በተዘጋጀው የሐዘን ዝግጅት ላይ፤ የአካባቢው ታጣቂዎች በሙሉ ለሐዘን መግለጫ የሚሆን ጥይት እንዲተኩሱ ታዘው በወቅቱ በተተኮሱ ጥይቶች፤ አንድ አዋቂ ወዲያውኑ ሲሞት አንድ ወጣት ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል እንደገባ ተናግረዋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናትም በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው፤ ህዝቡ በአቶ መለስ ሞት በከፍተኛ ሁኔታ በማዘኑ በተተኮሰው ጥይት ሰው እንደሞተና፤ የሰው መሞትም ይሁን መቁሰል ከሕዝቡ ሐዘን ብዛት የተከሰተ እንደሆነ አድርገው ገልፀዋል ብለዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ግለሰብ አክለውም፤ በሀዘን መግለጫው ዝግጀት ወቅት፤ የከተማው ታጣቂዎች በሙሉ እንዲተኩሱ፣ ያልተኮሱ የመሣሪያ አፈሙዝ እየተሸተተ መሣሪያውን እንዲያወርድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ እንደነበር ተናግረዋል።
በሀዘን ሥርአቱም ይሁን ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ቀናት አባይን የደፈረ፣ ኢትዮጵያን ያስከበረ ከሚለው መፈክር ጎን ለጎን ዋልድባንም የደፈረ ኢትዮጵያን ያሣፈረ የሚሉ መፈክሮችም ይሰሙ እንደነበር ተናግረዋል።
በሌላ ዜና በምሥራቅ ሸዋ ዞን በምትገኝ አንዲት ከተማ ለአቶ መለስ ዜናዊ በተዘጋጀ የሐዘን መግለጫ ለቅሶ ላይ ደረት ሲመቱ የዋሉ ወይዘሮ በዕለቱ ሕይወታቸው ማለፉንና የሞቱትም በልብ ድካም ሊሆን እንደሚችል መገመታቸውን ምንጮቻችን ከስፍራው ነግረውናል።