ነሀሴ ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር አንድ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነው የአቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ስነስርአት በርካታ አስገራሚ ነገሮችን እያሳየ በመጠናቀቅ ላይ ነው። እሁድ እለት አብያተ ቤተክርስቲያናት ለአቶ መለስ ልዩ የጸሎት ስነስርአት እንዲያዘጋጁ መታዘዙ በተሰማ ማግስት፣ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ አላግጣችሁዋል ወይም በደንብ አላዘናችሁም የተባሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ በርካታ ወጣቶች በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ (ማዕከላዊ)፣ ሰንዳፋ እና ሸዋሮቢት ተወስደው መታሰራቸውን የኢሳት የፖሊስ ምንጮቻች ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ወጣቶች አቶ መለስ ዜናዊ ለአገር የሰሩት ስራ ለም፣ የእርሳቸው መሞት ለኢትዮጵያ እረፍት ነው፤ የበሉት ሲያለቅሱ፣ ያልበላነው እንስቃለን የሚሉ ንግግሮችን እንደተናገሩ እንዲሁም ፎቷቸውን ለመስቀል እና ለቲሸርትና ለፎቶ የሚዋጣውን ብር በተቃውሞ አልተቀበሉም የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በሰንዳፋ የሚገኙ ብዙዎቹ እስረኞች በተበሳጩ ወታደሮች እንደተደበደቡ እና ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የሚካሄደውን የቀብር ሥነ-ስርዓት ለከፍተኛየኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ለክልል የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ለውጭ አገራት መሪዎች፣ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትና ለታዋቂ ሰዎች ደህንነት ሲባል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የደህንነት አባላት ለጥበቃ መመደባቸው ታውቋል። በከፍተኛ የደህንነት ጥበቃ ስነስርአቱን ለማካሄድ ለምን እንደተፈለገ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች በስነስርአቱ ላይ እንደሚገኙ መገለጡ ውጥረቱን ሳይጨምረው አልቀረም።
በርካታ የአዲስ አቅራቢያ እና አካባቢ ህዝቦች በአዲስ አበባ መግቢያ አራቱም በሮች ማለትም በኮተቤ፣ አየር ጤና፣ ሰሜን መዘጋጃ እና ፣ ቃሊቲ አካባቢዎች በተዘጋጁት ትላልቅ ሶኒክ ስክሪኖች የቀብር ሥነ- ስርዓቱን እንዲከታተሉ የተመቻቸ ሲሆን በመሐል አዲስ አበባም በፒያሳ በማዘጋጃ ቤት አቅራቢያ፣ በመገናኛ ፣ በአስኮ፣ በመስቀል አደባባይ እና በሌሎች ቦታዎች ዋልታ የኢንፎርሜሽን ማዕከል የሚቆጣጠረው የመረጃ መረብ ተተክሏል። የኢቲቪን የቀጥታ ሥርጭት የዋልታን ዶክመንተሪዎችና ልዩ ፕሮግራሞች ወደ ህዝቡ እንደሚያሰራጭ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች የተተከሉትን እና ቀደም ሲል የነበሩትን ትልልቅ ሶኒክ ስክሪን የመረጃ፣ የፕሮፓጋንዳ እና ማስታወቂያ ማስተላለፊያ ስክሪን የኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ክንፍ የሆነው ዋልታ የመረጃ ማዕከል በባለቤትነት በመቆጣጠር ይሰራባቸዋል ሲሉ ምንጮቻችን ገልጸው፣ ለዚህም ድርጊቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከመንግስት ካዝና ወጪ ተደርጎ እንደሚከፈለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን በሀዘኑ ምክንያት እንዳያስነግር በታዘዘበት በዚህ ወቅት የአቶ መለስን የዶክመንታሪ ስራዎች ሰርቶ ለኢቲቪ በማቅረብ ከፍተኛ የሆነ ገቢ የሚያስገኝ ስራ መስራቱ ታውቋል።
በተያያዘ ዜናም የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ማህበር የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስከሬን በሙዚየም እንዲቀመጥና በህይወት ዘመናቸው የሰሩት አኩሪ ስራ እንዲታወስ መጠየቁን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገበ።
ኢዜአ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አገሪቱ ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገብ በአለም አቀፍ ተጠቃሽ እንድትሆን የጣሩ መሪ በመሆናቸውና በህዝቦች ተፈቃቅሮና ተሳስቦ የመኖር ባህል በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ያደረጉ በመሆናቸው ማኅበሩ አስከሬናቸው ሙዚየም ይቀመጥ የሚል አቋም ይዟል ብሎአል።
አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እንድትሸጋገር ዕቅድ ያወጡና ኢንዱስትሪው መሪ እንዲሆን ብቁ አመራር የሰጡ በመሆናቸው ታሪካቸው ለትውልድ እንዲተርፍ አስከሬናቸው በሙዚየም እንዲቀመጥ የሚለውን ሃሳብ ህብረተሰቡ እንዲወያይበት እንጠይቃለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በምዕተ ዓመቱ ያገኘችው ታላቅ መሪ በመሆናቸው ህያው ስራቸው ለትውልድ መትረፍ አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቱ አስከሬናቸው በሙዚየም ቢቀመጥ ስራቸው ህያው እንዲሆንና ትውልድ እንዲማርበት እንደሚያደርግ ገልፀዋል እንደ ኢዜአ ዘገባ።
አስከሬኑ በሙዚየም የሚቀመጥ መሪ ለአገሩ ትልቅ እመርታን ያስገኘ ነው ያሉት አቶ ፋሲል እኚህ ታላቅ መሪ አገሪቱን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት ትልቅ ትግል ያደረጉና ትልቅ ዕቅድ ወይም መስመር የዘረጉ ባለ ራዕይ መሪ በመሆናቸው ይህ ይገባቸዋል ብለዋል።
የአስከሬኑ መቀመጥ መጪው ትውልድ የእሳቸውን አርአያ በመከተል መልካም ጅምሮችን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል አቅም እንዲፈጠር እንደሚያደርግም አክለዋል።
የአቃቂ ጋርመንትና ጂጂ ጋርመንት ስራ አስኪያጅና የማህበሩ የቦርድ አባል አቶ ጌታቸው ቢራቱ በበኩላቸው እንደተናገሩት የጥንት አባቶቻችን ”ከአይን የራቀ ከልብ ይርቃል” ይላሉ እኛም ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳይርቁና የእሳቸውን አርያነት እንድንከተል አስከሬናቸው በሙዚየም ይቀመጥ የሚል ሀሳብ አለን ማለታቸውን የመንግሰት የዜና ወኪል ገልጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንትና ለዚች አገር ነፃነት የተዋደቁ፣ ዛሬ ላይ ልማቷን አፋጥነው በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ ያደረጉና ለዚህች አገር የሞቱ በመሆናቸው የእኚህን ድንቅ መሪ አፅም አለም እንዲያየው ሙዚየም ቢቀመጥ ደስተኛ ነኝ ሲሉ አክለዋል።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የተፈለገው ደረጃ እንዲደርስና ዘርፉ ያለበት ችግር እንዲወገድ ሌት ቀን ከእኛ ጋር ሲሰሩ የኖሩ በመሆናቸውና በማለፋቸው ከፍተኛ ሃዘን ቢሰማንም ህያው እንዲሆኑ አስከሬናቸው ሙዚየም ይቀመጥ የሚለው የማህበሩ አባላት ሃሳብ ነው ያሉት የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሶሎኔስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ታዬ ናቸው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በእምነታቸው ያልጠነከሩና በመንፈሳዊ ዕውቀት ያልታነጹ እንዲሁም በጥቅም እና በዘር የተጋረዱ አንዳንድ ወገኖች ሰሞኑን በአቶ መለሰ አስከሬን ፊት ወድቀው ሢሰግዱ የተስተዋለ ሲሆን፤ የሥርዓቱ አገልጋዮችም ይህንኑ ትዕይንት በካሜራቸው እያስቀሩ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ባለፉት 21 ዓመታት የአቶ መለስ አስተዳደር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ታፍነው መጥፋታቸውን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎች ለእስራት፣ለግርፋትና ለስደት መዳረጋቸውን እና ሌሎችም እጅግ ዘግናኝ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ለ9 ዓመታት በ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የሰሩት አቶ ያሬድ ሀይለማርያም አጋልጠዋል።
አቶ ያሬድ ፦”የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ” በሚል ርዕስ ይፋ ባደረጉት “ዶክመንት” በአቶ መለስ አመራር የተፈፀሙትን አስከፊ የጭካኔ ተግባራት በፎቶና በስም ዝርዝር ጭምር አመላክተዋል።
የዋልታ ማእከል ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተተካ በቀለ ለሰራተኞቻቸው ባደረጉት ንግግር ደግሞ “በምንወዳቸው መሪያችን ሞት ልባችን ቢሰበርም ወደ ኋላ ተመልሰን ድህነት ውስጥ እንደማንገባ እርግጠኞች ነን ብለዋል።” አቶ ተተካ ገልፀዋል።
በአለም ላይ በድህነት የነበሩ ሀገራት ከፍፁም ድህነት ወደ ፍፁም ብልፅግና የተሸጋገሩት ጥቂት ባለ ራዕዮች ያፈለቁትን ሀሳብ ቀጣዩ በትውልድ ውስጥ እየተቀባበለ እንዲሄድ በማድረግ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም በኢትዮጵያ ባለው ትውልድ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፅናትን፣ ህዝብ መውደድንና ለአላማ መኖርን ያስተማሩ ታላቅ መሪ ነበሩ ያሉት ስራ አስኪያጁ ለመጪው ትውልድ ለኑሮ የምትመች ሀገር ፈጥረውልናል ብለዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide