የአብዲ ኢሌ የደህንነት አባላት በዱልሚዲድ አመራር ላይ ያደረጉት የአፈና እርምጃ ከሸፈ

የአብዲ ኢሌ የደህንነት አባላት በዱልሚዲድ አመራር ላይ ያደረጉት የአፈና እርምጃ ከሸፈ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ/ም) ትናንት ምሽት የአብዲ ኢሌን ፍጹማዊ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በመቃወም ዱል ሚዲድ እየተባለ በሚጠራው በኢትዮ-ሶማሊ ተወላጆች የተቋቋመውን ድርጅት ከሚመሩት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑትን አቶ ካድር አዳንን ከአዲስ አበባ ወደ ጅግጅጋ አፍኖ ለመውሰድ የተደረገው ሙከራ በፌደራል የደህንነት መስሪያ ቤትና በአሜሪካ ኢምባሲ አማካኝነት ሊከሽፍ ችሎአል።
አቶ ካድር ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ለዲያስፖራው ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ወደ አገራቸውን በቅርቡ የገቡ ናቸው። አፈናውን ለማካሄድ ከተላኩት የደህንነት አባላት መካከል የጄ/ል ገብሬ ዲላ ቀኝ እጅ የሆነው ሃሰን አህመድ የሚገኝበት ሲሆን፣ ሌሎች አፋኞች ደግሞ በማምለጣቸው ክትትል እየተደረገባቸው ነው።
አብዲ ኢሌ ለአፈና ያሰማራው ሀሰን አህመድ በተለምዶ ሀሰን ገብሬ የሚባለው ግለሰብ በሱማሌዎችና በኦሮሞዎች ዘንድ ተደጋጋሚ አፈናዎችንና ግድያዎችን ከማካሄዱም ባሻገር ፣ ናይሮቢ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኛ ሆኖ በሰራበት ወቅትም ለበርካታ ለኦሮሞና ሶማሊ ተወላጆች ግድያና አፈና ተጠያቂ ነው።
ከአፈና እቅዱ ጀርባ ጄኔራል ገብሬ እንዳለበት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ። አቶ ካድር በሰጡት መግለጫ፣ እንዲህ አይነቱ የአፈና ሙከራ በእርሳቸው ላይ እንዲያበቃ ጠይቀዋል። አፈናው እንዲጨናገፍ ላደረጉት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው ስለ አፈናው ሂደት ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጡ ተናግረዋል። በጉዳዩ ዙሪያ በመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።