(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2010) የሕወሃት መሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ስልጣን ለማዳከም የተለያዩ እቅዶችን መንደፋቸው ተገለጸ።
ሰሞኑን በትግራይ በተካሄደውና በመከላከያ ውስጥ ያሉ ነባር የሕወሃት የሰራዊት አባላት በተሳተፉበት ሚስጥራዊ ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያን እንዳይቆጣጠሩና በክልሎች የሚኖራቸውን ስልጣን የሚገድቡ የተለያዩ ርምጃዎች ተወስደዋል።
ከመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች የተገኙበትና በአቶ አባይ ጸሀዬና በአቶ በረከት ስምኦን የተመራው ስብሰባ የትግራይ ተወላጆች ከስልጣን ተገፍተዋል የሚል ክርክርም ተነስቷል።
የህወሃት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች በመሩትና በመከላከያ ውስጥ የሚገኙ ነባር የህወሃት የሰራዊቱ አባላት ብቻ በተሳተፉበት በዚሁ ሚስጢራዊ ስብሰባ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን በተመለከተ ጠንካራ ክርክር መደረጉን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
ከሰራዊቱ አባላት በዋናነት የተነሳው ጥያቄ የትግራይ ተወላጆች ከፌደራል መንግስቱ የስልጣን ቦታዎች ተገፍተዋል የሚል ነበር።
ከመድረክ በተሰጠው ምላሽም በፌደራል ደረጃ ስላለው የስልጣን ምደባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈለገውን ሰው ሊመድብ ይችላል ውናው ነገር እነዚህ የተመደቡት ሰዎች ከህወሀት አቅጣጫና ፍላጎት ውጭ መሆናቸውን እየተከታተልን ነው።
እንደዚያ ከሆነ የማንቀበል መሆኑ አሳውቀን የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
የትግራይ የበላይነት አለ የሚለውን ክስ ለማጥፋት የሚጠቅመን እንዲሆን እናደርጋለን፣ ከእነ አሜሪካ የሚመጣውንም ጫና ለመቀነስ አሁን ያለውን ምደባ መቀበሉ የሚያዋጣን ነው የሚል ምላሽ የሰጡት አቶ አባይ ጸሀዬ ከዚያ ውጭ አሁንም ቁልፍ ቦታዎችን በበላይነት የምንቆጣጠረው እኛ መሆናችንን እናረጋግጥላችኋለን ሲሉ ተናግረዋል።
በስበሰባው የተገኙት የህወሀት መሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ስልጣን ለማዳከም ማቀዳቸውን የሚያሳይ መግለጫም ለተሰብሳቢዎቹ አቅርበዋል።
በፌደራል መንግስቱ ላይ ስልጣኑ ቢኖርም ወሳኙ ክልሎችን መቆጣጠር በመሆኑ በክልል ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኖራቸውን ስልጣን እንገድበዋለን ማለታቸውም ተጠቅሷል።
ስለትግራይ ክልል ተነስቶም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትግራይ ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ ከወዲሁ ዶክተር ደብረጺዮን ወደ ትግራይ እንዲመጡ አድርገናል፣ ትግራይ ላይ ማንም ዘሎ የሚወስንበት ዕድል የለም፣ በሌሎችም ክልሎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የማዘዝ ስልጣን የሚገድብ ርምጃ ይወሰዳል ሲሉ መግለጻቸውን የኢሳት ምንጮች ከላኩት መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ዝርዝሩ ባይታወቅም የፌደሬሽን ምክር ቤት ክልሎች እርስ በእርስ የሚኖራቸውንና ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚወስን አዋጅ ማጽደቁ ዛሬ ተገልጿል።
የህወሀት መሪዎች ለነባር ታጋዮች በትግራይ ቃል ከገቡትና የጠቅላይ ሚኒስትሩን በክልሎች የሚኖራቸውን ስልጣን ለመገደብ ከገለጹት እቅዳቸው ጋር የሚገናኝ ሊሆን እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
የህወሀት መሪዎች በትግራዩ ሚስጢራዊ ስብሰባ ላይ ያነሱት ሌላው ቁልፍ ጉዳይ መከላከያ ሰራዊቱ ነው።
ዶክተር አብይ መከላከያውን ማዘዝ እንዳይችሉ የማድረጉ ስራ ቀድሞ የተጠናቀቀ ነው የሚል ምላሽ ከመድረክ ተሰጥቷል።
የአሁኑ መከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙትም ሆኑ የደህንነት አማካሪው አቶ አባዱላ ገመዳ ከአስተዳደር ስራ ውጭ እጃቸውን እንዳያስገቡ የሚደረግ በመሆኑ ለህውሀት እንደስጋት መታየት የለባቸውም ሲሉ የመከላከያ አዛዦች ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል።
ግፊት ቢመጣ እንኳን ቀድመን የመከላከያ ቁልፍ ክፍሎችን ወደ ትግራይ በማምጣታችን ከእኛ እጅ ሌወጣ አይችልም በማለት በመከላከያ ውስጥ ላሉ ነባር የህወሀት ሰራዊት አባላት ምላሽ ተሰጥቷል።
ዋና ዋና የሚባሉት የመከላከያ ክፍሎች ማለትም አየር ሃይል፣ የመካናይዝድ ሃይል፣ የመረጃና መገናኛ መምሪያዎች ወደትግራይ እንዲመጡ በመደረጉ ስጋት ሊገባን አይገባም ሲሉ አመራሮቹ መግለጻቸውን ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።