መጋቢት ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ክልል አቀፍ የእምቦጭ አረም አስወጋጅ ዩኒት አስተባባሪ ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት ወ/ሮ በፍታ ጥሩነህ ሰሞኑን ለመንግስት ሚዲያዎች እንደተናገሩት የአረሙ ስጋት በጣም ሠፊ በመሆኑ ተስፋ የተጣለበት ይህ ትልቅ ግድብ በእንቦጭ አረም ሊጠቃ እንደሚችል ስጋቱ ከፍተኛ መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡
ዩኒት አስተባባሪዋ ስለመጤ አረሙ ሲያስረዱ የውሀን ተፈጥሯዊትነት በማዛባት እንዲደርቅ የሚያደርገው እምቦጭ ወይም ዋተር ሐይሲን በመባል የሚታወቀው መጤ አረም፤ በአማራ ክልል በተለይም በጣናና በዙሪያው በሚገኙ ቀበሌዎች ከፍተኛ ጉዳት እያደረሠ ነው፡፡ ይህ አረም አብዛኛውን ጊዜ ረግረጋማ ቦታዎችን፣ ወንዞችን፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦችንና የመስኖ ቦዮችን በማጥቃት ከፍተኛ ችግር በአካባበቢው አርሶአደሮችና አሳ አስጋሪዎች ላይ በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡
የመስኖና የሀይል ማመንጫ ግድቦች ሳይቀሩ አደጋ ተደቅኖባቸዋል። በዚህ ዓመት አረሙ በአባይ ወንዝ ላይ ተከስቶ መገኘቱ የስጋታቸው መነሻ መሆኑን ባለስልጣኗ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ወደ አባይ ወንዝ ገባ ማለት በቀጥታ ወደ አባይ ግድብ ገባ ማለት እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ በፍታ ዓባይ ወራጅ ውሀ በመሆኑ አረሙ እስካሁን ወደ ግድቡ ገብቷል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
“በአባይ ግድብ አካባቢ ቢፈተሽ አደገኛው አረም አይጠፋም” በማለት የተናገሩት አስተባባሪዋ፣ “ለግድቡ ግንባታ አሸዋ የሚጫነው በጐንደር ዙሪያና በሊቦ ከምከም አካባቢዎች ነው፡፡ እነዚህ አካባቢዎች በእምቦጭ የተወረሩ ናቸው፡፡ ይህ እንዳይሆን ለክልሉ አመራሮች ብዙ ጊዜ ባሳስብም ሰሚ ባለማግኘቴ ዝምታን መርጫለሁ” ሲሉ አጋልጠዋል።
ከአሸዋ ጋር ተጭኖ የመግባት ሠፊ ዕድል አለው፡፡ ነገ ውሀው ሲገደብና አረሙ ሲፈጠር አርመን እንኳ አንጨርሠውም፡፡ ከምናስወግደው ይልቅ የአረሙ የመስፋፋት ፍጥነት ይበልጣል” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
አረሙ ከታረመ በኋላ እዚያው ስለሚወድቅ መከላከሉን አስቸጋሪ እንዳደረገው የሚናገሩት አስተባባሪዋ በዚህ ምክንያት በጣና ሀይቅ ዙሪያ የነበሩ ደንገሎችና የሳር ዝርያዎች ጠፍተዋል፣ የአሣ ሀብቱም ተመናምኗል፡፡
በ2008 ዓም ደግሞ ድርቅ በመከሠቱ አብዛኛው አረም የጠፋበት ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት ወ/ሮ በፍታ ሽፋኑ ከአምስት ሺህ ሄክታር ተነሰቶ በዚህ ዓመት 24 ሺህ ሄክታር ሸፍኖ ተገኝቷል፡፡
አስተባባሪዋ አክለውም “ከአረሙ ባህሪ አንፃርም ዘላቂ መፍትሄ እስካሁን አልተገኘም፡፡ አርሦ አደሩ በዚህ የተነሣ ተሠላችቷል፡፡ “ ብለዋል። አርሶአደሮች ሁሌም ‹በየዓመቱ እያረምን እስከመቼ እንዘልቃለን?› የምርት ጊዜያችንን ተሻማብን፣ አረሙን ለማረም ወደ ውሀው ስንገባም ለበሽታ ተጋለጥን› እያሉ እንደሚናገሩ የገለጹት ሃላፊዋ፣ “ጣና ባለቤት አልባ ሆኗል፡ እምቦጭ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ በጣና ዙሪያ ብዙ ሰውሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች አሉ፡፡ ይህንን የሚቆጣጠር አካል መኖር አለበት፡፡ “ ሲሉ አክለዋል።
በተለያዩ ደረጃ ያሉ የክልሉ አመራሮች አረሙ ስላለበት ሁኔታ አለማወቃቸውንም ሃላፊዋ አጋልጠዋል። “የፌዴራል መንግስት ችግሩን ያውቀዋል” የሚሉት አስተባባሪ አስራ አምስት የሚደርሱ ሚኒስቴር መስሪያቤቶችን ያሳተፈ ውይይት ቢደረግም ትኩረት መስጠት ቀርቶ ዘወር ብለው አላዩትም፡፡ እንመድባለን ያሉትን 15 ሚሊዮን ብር በጀት እንኳ አልፈቀዱም፡፡ በጣና ዙሪያ የተከሠቱ አረሞችን ለማስወገድ ወደ 14 ቢሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ ይህም ጥናት ለደን ሚኒስቴር ቢላክም እስካሁን ምንም ምላሽ እንደሌለ አስተባባሪዋ ተናግረዋል።
የኢሳት የክልሉ ወኪል ከአመታት በፊት የአረሙን አደገኛነት በተመለከተ ተደጋጋሚ ዘገባ ማቅረቧ ይታወቃል።