የአባይ ግድብ መሰረቱ ችግር ሊኖረው ይችላል ተባለ

መስከረም ፳፬(ሃያ አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ብሉበርግ የአለማቀፍ አጥኚዎች ቡድንን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው መንግስት በማስገንባት ላይ ያለው የአባይ ግድብ መሰረቱ ችግሮች ሊኖሩበት ስለሚችል መንግስት እንደገና እንዲያስጠና መክሯል።

ግድቡ በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በደንብ መጠናት አለበት ሲሉ የባለሙያዎቹ ቡድን አስተያየቱን ሰጥቷል።

የግድቡን መሰረት ለማጠንከር መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል በማለት ያመለከቱት ባለሙያዎች፣ “ድክመት ቀጠና ”  ተብሎ በተለየው አካባቢ ያለው ድንጋይ እንደገና ሊፈተሽ እንደሚገባው መክረዋል።

ይህ የጥናት ቡድን በኢትዮጵያ ሀሳብ አመንጭነት የተቋቋመ  ሲሆን፣  ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽና ሱዳን ሁለት ሁለት ባሙያዎች ከሌሎች አገራት ደግሞ አራት ባለሙያዎች ተካተውበታል። እስካሁን ይፋ ያልወጣው ሪፖርት ለሶስቱ መንግስታት መላኩንም ብሉምበርግ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ቀደም የጥናት ቡድኑ ያቀረበው ሀሳብ ግድቡ ምንም ጉዳት እንደማያመጣ ያረጋገጠ ነው በማለት ይፋ ማድረጋ ይታወሳል።

አሁን የቀረበው አዲስ ጥናት ግን ግድቡ የግብጽን የውሀ አቅርቦትና የሀይል አቅርቦት የሚቀንስ መሆኑን የሚያመለክት ነው።

የጥናት ቡድኑ ያቀረባቸውን አስተያየቶች ኢትዮጵያ ትቀበላቸው አትቀበላቸው እንዲሁም ስራው ተቋርጦ እንደገና  ጥናት ይካሄድ አይካሄድ በዘገባው የተጠቀሰ ነገር የለም። የኢትዮጵያ መንግስት የግድቡን 30 በመቶ ማጠናቀቁን መናገሩ ይታወሳል።

በካርቱም  አካባቢ የሚኖሩ ነዋረዎች ግድቡ አደጋ ቢያጋጥመው ካርቱምን አስራ አምስት ሜትር ድረስ  እንደሚያሰጥም በስጋት እየተናገሩ ሲሆን በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ላይ ያላቸውን የብቃት ጥርጣሬ እየተናገሩ መሆኑን ወኪላችን ከካርቱም ዘግባል:: ይሁን እንጅ የአልበሽር መንግስት በይፋ ግድቡን መደገፉ ይታወቃል።

የእትዮጵያ መንግስት የጀመረው የግድብ ግንባታ በተለይ በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው ቆይቷል።