ኢሳት (የካቲት 25 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ የነበረው የአሽከርካሪዎችና የመኪና ባለቤቶች የስራ ማቆም አድማ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተጠናክሮ ቀጠለ።
የኢሳት ምንጮት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የላኩልን መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞች የስራ ማቆም አድማው አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል።
በዛሬው እለት በኦሮሚያ ነቀምት ከተማ የተካሄደው አድማ ግጭቶችን ያስከተለ ሲሆን የመንግስት ሃይሎች በከፈቱት ተኩስ የከተማው ህዝብ ከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቁን ለማረጋገጥ ተችሏል። የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ የቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ አድማ የመቱ ሹፌሮችን እና የአሽከርካሪ ባለቤቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አጠናክረው ቀጥለዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴ፣ ባቲ፣ አጣዬ፣ እና ቆቦ ከተሞች የአሽከርካሪዎችና የመኪና ባለቤቶች ያደረጉት የስራ ማቆም አድማ አርብ ለሶስተኛ ቀን ቀጥሏል። የክልል የጸጥታ ሃይል እና የአካባቢው አስተዳደር የአሽከርካሪዎችን ባለቤቶች አግባብቶ ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የአካባቢው ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።
እያገባደድን ባለነው ሳምንት መጀመሪያ የአዲስ አበባ፣ በወልዲያ፣ በአሰላ፣ በባሌ ሮቤ፣ በመሳሰሉ ከተሞች የስራ ማቆም አድማ መደረጉ ይታወሳል።