የአሸንዳ በዓልን በጭፈራ ሊያሳልፉ የነበሩ የህወሃት ደጋፊዎች ተቃውሞ ገጠማቸው፥ በመንግስት ሃይሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ገንዘብ ተሰበሰበ

ኢሳት (ጳጉሜ 1 ፥ 2008)

በካናዳ ካልጋሪ የአሸንዳ በዓልን በደስታና በጭፈራ ለማሳለፍ የሞከሩ የህወሃት ደጋፊዎች በአካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ገጠማቸው።

ኢትዮጵውያኑ ባለፈው ቅዳሜ ተቃውሟቸውን ያሰሙት በአሁኑ ወቅት በአገራችን በርካታ ሰዎች በአጋዚ ወታደሮች እየተገደሉና እየተጨፈጨፉ በደስታ መጨፈር ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን በቁጭት በመግለጽ ነው።

በአሰቃቂ ሁኔታ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በአጋዚ ታጣቂዎች የተገደሉ ሰዎችን ፎቶ በመያዝ ኢትዮጵያውያኑ የህወሃትን ደጋፊዎች ድርጊት አውግዘዋል።

ተቃውሞ የገጠማቸው የስርዓቱ ደጋፊዎች የፖሊስ ጥበቃ ቢደረግላቸውም፥ በቁጭት ያዘኑት ኢትዮጵያውያን የአዳራሹን በር ጥሰው በመግባት ስነስርዓቱ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

በሌላ በኩል  ቦስተን- ማሳቹሴት ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያውያን “ለወገን ጥሪ ከወገን ምላሽ” በሚል መሪ ቃል በተደረገው ታላቅ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በመንግስት ሃይሎች የተገደሉትን ሰለባዎችን በማሰብ ቁጣቸውን ገልጸዋል። በዚሁ ጊዜም ነጻነት ላጣው ወገናቸው ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ከዘጠና ሽህ ዶላር በላይ ማሰባሰባቸውን ለኢሳት የደረሰው ዘገባ ያስረዳል።

በዝግጅቱ አርቲስት ታማኝ በየነ እና ድምፃዊ ፋሲል ደመወዝ በመገኘት ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል::

የተሰበሰበው ገንዘብም በግሎባል አልያንስ በኩል ለተፈለገው አላማ እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል:: የቦስተንና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለወደፊቱ በሚደረጉ አገራዊ ድጋፎች አጋር መሆናቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።