የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ለተፈጸመባት ኢትዮጵያዊት የ150 ሺ ዶላር እንዲከፈላት ተወሰነ

ኢሳት (መጋቢት 2 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ከአመታት በፊት የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ለተፈጸመባት ታዳጊ ወጣት ህጋዊ መብቷን በአግባቡ አላስቀመጠም በሚል የ1500 ሺ ዶላር (3 ሚሊዮን ብር በላይ) ካሳ እንዲከፍል የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ወሰነ።

ከአስር አመት በፊት በ13 አመቷ ታዳጊ ላይ ድርጊቱን የፈጸመው አብረው ጅማ ንጉሴ ጥፋተኛ መሆኑ ቢረጋገጥም ተበዳዩዋ ልጅአገረድ አይደለችም የሚል ይግባኝ ቀርቦ ክሱ ፍትህ ሳያገኝ መቅረቱን BBC ዘግቧል።

ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ድርጊቱ የሃገሪቱን እና የአለም አቀፍ ህግን የሚጻረር ነው በማለት አቤቱታቸውን ለአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ለተበዳዩዋ ወጣት የ150 ሺ ዶላር ካሳን እንዲከፍል ወስኗል።

መቀመጫውን በጋምቢያ ያደረገው ፍርድ ቤቱ መንግስት በደል የተፈጸመባትን ታዳጊ ወጣት መብቷን በአግባቡ አላስጠበቀም፣ ተገቢውን የፍርድ ሂደት እንድታገኝ አላደረገም የሚሉ ምክንያቶች በመስጠት የፍርድ ሂደት እንድታገኝ አላደረገም የሚሉ ምክንያቶችን በመሽተት ፍርድ ማስተላለፉ ታውቋል።

የታዳጊዋ ወጣቷን ጉዳይ ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ሲከታተል የቆየውና (Equality Now) የተሰኘ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅት ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ለሌሎችም መልዕክትን የሚያስተላልፍ ነው ሲል መግለጹን BBC በዘገባው አመልክቷል።

በታዳጊ ወጣቷ ላይ የአስገድዶ መድፈርን ድርጊቱን የፈጸመውን አብረው በዋስ ከተለቀቀ በኋላ ወጣቷን በድጋሚ ለአንድ ወር በማገት አስገድዶ የጋብቻ ሰነድ ማስፈረሙንም ለመረዳት ተችሏል።

ተከሳሹ ከአራት ግብረ አበቶቹ ጋር ለፈጸመው ድርጊት የ10 አመት የእስር ቅጣት ተላልፎበት የነበረ ቢሆንም፣ ይግባኝ አቅርቦ መለቀቁን BBC ባቀረበው ሪፖርት አስነብቧል።

ይህንንም ተከትሎ ለሴቶች መብት መከበርና ጥቃት እንዲቆም የሚታገለው የሰብዓዊ መብት ተቋም ጉዳዩን ወደበላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ ቢዘገይም ፍትህ ማግኘቱን የዜና ወኪሉ አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት እድሜዋ በ20ዎች ውስጥ የሚገኘው ተበዳይ ከቤተሰቦቿ ጋር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝና ትምህርቷን በመከታተል ላይ መሆኗንም ከድርጅቱ ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።