የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ተከትሎ የታፈሱት ወጣቶች ይፋዊ ባልሆኑ እስር ቤቶች ታስረዋል

ኅዳር ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ተከትሎ ከተለያዩ  የሃገሪቱ ስፍራዎች ታፍሰው የታሰሩት እስረኞች ገሚሶቹ በአዋሽ አርባ፣ በኦሮሚያ ፖሊስና በቀድሞው ህጻናት አምባ አሁን አላጌ የግብርና ኮሌጅ በመባል በሚጠራው ስፍራ እንደሆነ ታውቋል። መንግስት አዋጁን ለማስከበር በሚል ከ20ሺ እስከ 30ሺ ይደርሳል ተብሎ  የሚገመቱ ታሳሪዎችን ቤተሰብና ዘመድ ሊያውቀው በማይችልበት ስፍራ ወስዶ ማሰሩ በታሳሪዎቹ ላይ የስነ ልቦና ጫና ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ብዙዎች እየገለጹ ይገኛሉ። የእስረኞቹ አያያዝ ምን እንደሚመስል እስካሁን ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን፣ በ1997  ዓም በደዴሳ የቀድሞ ጦር ካምፕና በመሰል ስፍራዎች ለተደረጉ የጅምላ  እስር የተዳረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ተፈጸሞ  የነበረው ዓይነት ኢ ሰብአዊ የእስረኞች አያያዞች ሳይፈጸሙባቸው እንደማይቀር መረጃውን ያቀበሉን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

በ1997 ዓም ተካሂዶ የነበረውን ብሄራዊና ሃገር ዓቀፋዊ ምርጫን ተከትሎ በተወሰደ የጅምላ እስር ሰለባ የሆኑ ታሳሪዎች ላይ ከምግብና ውሃ አቅርቦት ጀምሮ ጭካኔ  የተሞላበት አያያዝ መያዛቸውን እንዲሁም አንዳንዶቹ የመብት ጥያቄ በመጠየቃቸው በእስረኞች ፊት እንዲረሸኑ መደረጉን ጭምር የሚገልጹ መረጃዎችን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ አካላት ሲገልጹ እንደነበር የሚታወስ ነው።