የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ የአፈናና ጭቆናን ሊያስፋፋ ይችላል ሲል ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ዘገበ

ኢሳት (ጥቅምት 10 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሃገሪቱ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ የአፈና እና ጭቆናን ሊያስፋፋ ይችላል ሲል በብሪታኒያ ተነባቢ የሆነው ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ዘገበ። በወቅታዊ የሃገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ልዩ ሪፖርትን ያቀረበው ጋዜጣው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር በወሰደው የሃይል ዕርምጃ በአመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉን አውስቷል።

ህዝባዊ ተቃውሞችን ለመቆጣጠር ለበርካታ ወራቶች ሲካሄዱ የነበሩ እርምጃዎችን ውጤት ባለማምጣታቸው ምክንያት መንግስት እንቅስቃሴውን በተጠናከረ መልኩ ለማስኬድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ማድረጉን ጋዜጣው አስነብቧል።

በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት አሁን ይዞ ያለውን አቋም የማያሻሽል ከሆነ ሃገሪቱ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ወደማይችል አለመረጋጋት ልታመራ እንደምትችል አለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ሃሰን ሁሴን ለጋርዲያን ጋዜጣ ገልጸዋል።

ሃሙስ በፓርላማ የጸደቀን አዋጅ አስመልክቶ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ዕርምጃው የሰብዓዊ መበት ረገጣን ሊያባብስ ይችላል ሲሉ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ቅሬታን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

በዚህ የፖለቲካ ውጥረት ዙሪያ ሰፊ ዘገባን ያቀረበው የብሪታኒያው አለም አቀፍ ጋዜጣ ትችትን እያስተናገደ ያለው አዋጅ በአደጋ ውስጥ ትገኛለች ያላትን ኢትዮጵያ ወደ ከፋ የፖለቲካ ውጥረት ሊያመራት እንደሚችል በሪፖርቱ አቅርቧል።

ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ እና በተቃዋሚ ተሳታፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው የተጀመረው ትግል መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ቢሆንም ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ለዘጋርዲያን ጋዜጣ አስረድተዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የቤት ለቤት ፍተሻን ጨምሮ የጅምላ እስር እየተፈጸመ መሆኑን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ። የብሪታኒያ ማሰረጫ ጣቢያ (BBC) የአዋጁን መውጣት ተከትሎ ከ1ሺ 600 በላይ ሰዎችን ለእስር መዳረጋቸውን ሃሙስ ዘግበዋል።