ኢሳት (ታህሳስ 10 ፥ 2009)
ከአስቸኳይ አዋጁ ተግባራዊ መደረግ በኋላ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ20ሺ መብለጡ ተገለጸ። ከመካከላቸው 20 ያህል የጸጥታ ሰራተኞች እንደሚገኙበት መንግስት አስታውቋል።
ለእስር የሚደረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ ከወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት በተጨማሪ የተለያዩ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለጊዜያዊ እስር ቤት እየዋሉ መሆኑንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት ለመቆጣጠር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በመጀመሪያው ዙር የእስር ዘመቻ ከ11 ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ባለፈው ወር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ በሳምንቱ መገባደጃ መግለጫን የሰጡት የኮማንድ ፖስቱ ሃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ በሁለተኛው ዙርን ተመሳሳይ ዝመቻ 12 ሺ 500 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በሁለቱ ዙሮች በአጠቃላይ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ20ሺ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ዙሪ ለእስር ተዳርገው ከነበሩት ከ11ሺ በላይ ሰዎች መካከል 2ሺ 449 የሚሆኑት ክስ እንደሚመሰረትባቸው አቶ ሲራጅ ተናግረዋል።
ይሁንና ክስ ይመሰረትባቸዋል የተባሉ ታሳሪዎች ከምን ወንጀል ጋር በተያያዘ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ሃላፊው የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ በሁለተኛ ዙር ለእስር ከተዳረጉት መካከልም ክስ የሚመሰረትባቸው እንደሚኖር ተመልክቷል።
በተለያዩ እስር ቤቶችና ጊዜያዊ ማቆያዎች ውስጥ ከሚገኙት እስረኞች መካከል 18 የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የኮማንድ ፖስቱ ሃላፊ አቶ ሲራጅ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ይሁንና የጸጥታ ሃይሎች በምን ምክንያት ለእስር እንደተዳረጉ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ለእስር የሚደረጉ ሰዎች እንዳሉ በተለያዩ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ ለእስር የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ መደበኛ እስር ቤቶች ከአቅም በላይ በመሙላታቸው ምክንያት በርካታ ወታደራዊ ማሰልጠኛና የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለጊዜያዊ እስር ቤት እየዋሉ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መውጣት ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸመባቸዋል የሚል ስጋት መኖሩን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ይህንኑ አዋጅ ጥሰው ተገኝተዋል ተብለው በቅርቡ ለእስር የተዳረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ፍ/ቤት በቅረቡ ጊዜ በሰንሰለት ታስረው እንደነበር እማኞች አስረድተዋል።