ኢሳት (ሚያዚያ 17 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ለተጨማሪ ወራቶች ተራዝሞ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአምቦ ከተማና አካባቢዋ ውጥረት ማንገሱን ዘ-ኢኮኖሚስት መጽሄት ዘገበ።
በሃገሪቱ ወቅታዊ ጸጥታ ዙሪያ ሰኞ ሪፖርትን ይዞ የወጣው አለም አቀፍ መጽሄቱ በከተማዋ የሚገኘው የአምቦ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ወታደራዊ ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስነብቧል።
ባለፈው አመት በአምቦ ከተማና ዙሪያዋ በሚገኙ የገጠር መንደሮች ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ያወሳው ዘ-ኢኮኖሚስት መጽሄት በከተማዋ አሁንም ድረስ ውጥረት መኖሩን የሚያሳዩ ነገሮች እንዳሉ በከተማዋ ያካሄደው ትዝብት አስደግፎ በሪፖርቱ አስፍሯል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ በሃገሪቱ አንጻራዊ መረጋጋት መታየት ቢጀምርም በኦሮሚያ እንዲሁም በአማራ ክልሎች የሚገኙ በርካታ ወጣቶች አዋጁ ሲጠናቀቅ ተቃውሞን ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው መረዳቱን ዘግቧል።
ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ባለፈው ወር በተመሳሳይ መንገድ ባቀረበው ዘገባ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት ተከትሎ ተቃውሞን ለመቀጠል ፍላጎት አላቸው ሲሉ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል። የአዋጁን ተግባራዊነት የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርቱ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች አሁንም ድረስ አለመረጋጋት በመኖሩ አዋጁ ይራዘም ሲል ጥያቄን አቅርቦ አዋጁ ለአራት ወር እንዲራዘም ተደርጓል።
ይኸው እስከ ነሃሴ ወር ድረስ ቀጣይ የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይ ተደጋጋሚ ተቃውሞን ስታስተናግድ በቆየችው የአምቦ ከተማ ውጥረትን አንግሶ እንደሚገኝ ዘ-ኢኮኖሚስት መጽሄት ዘግቧል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት ከዴሞክራሲ በፊት ልማትን የሚያስቀድም ፖለቲካዊ ሂደትን በመከተል ላይ እንደሆነ የተለያዩ ማሳያዎችን በማቅረብ በዘገባው አስፍሯል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣትን ተከትሎ መንግስት በተለይ ለወጣቶች የስራ እድልን ለመፍጠር ቃል ቢገባም፣ ከዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎች በሙያቸው ስራ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው መጽሄቱ አመልክቷል።
ለደህንነቱ ሲል ስሙን መግለፅ ያልፈለገ አንድ የአካውንቲንግ ምሩቅ በሙያው ስራ ለማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት በአንድ ሆቴል ውስጥ በገንዘብ ያዥነት እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት ፖለቲካዊ ተሃድሶን እንደሚያካሄድ ቃል ቢገባም እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከቦታቸው አለመነሳታቸውን ዘኢኮኖሚስት መጽሄት በዘገባው አስነብቧል።
በሃገሪቱ ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ 669 ሰዎች መሞታቸውን መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት ማመልከቱ ይታወሳል።
ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት ይፋ ያደረገው የሟቾች ቁጥር አነስተኛ መሆኑንና ድርጊቱ በገለልተኛ አካል መመርመር እንዳለበት በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎች ድርጊት ለመመርመር ጥያቄ ቢያቀርቡም መንግስት ጥያቄውን እንደማይቀበል ምላሽን ሰጥቷል።