ኢሳት (ህዳር 1 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቱሪዝም ገቢ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ተከትሎ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ተወካዮች ወደ ብሪታኒያ መጓዛቸው ተገለጸ።
መቀመጫቸውን በብሪታኒያ ያደረጉ በርካታ አለም አቀፍ አስጎብኚ ተቋማት በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ይኸው አዋጅ፣ በጎብኚዎች ላይ የደህንነት ስጋት አሳድሯል በማለት ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉ የነበረውን ጉብኝት መሰረዛቸው ይታወሳል።
የአስጎብኚ ድርጅቶቹ የወሰዱት ዕርምጃ በቱሪዝም ገቢው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።
ሃገሪቱ በዘርፉ እያጣች ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እልባት ለማፈላለግ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ተወካዮች ወደ ብሪታኒያ በመጓዝ በአንድ አለም አቀፍ የቱሪዝም መድረክ ላይ የማግባባት ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ዩሮ ኒውስ (Euronews) ዘግቧል።
ሳጋ፣ ኩኦኒ፣ እና ኮክስ፣ እንዲሁም ኪንግስ የተሰኙ ግዙፍ የብሪታኒያ የአስጎብኚ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ሊያደርጉ የነበሩትን የጉብኝት ስራ ከሰረዙት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ቴሌግራፍ የተሰኘ ጋዜጣ በቅርቡ ዘግቧል።
የብሪታኒያ መንግስት በተደጋጋሚ እየወጣ ያለው የጉዞ ማስጠንቀቂያ መረጃ የጉብኝት ፕሮግራማቸውን እንዲሰርዙ ምክንያት መሆኑን የብሪታኒያዎቹ የቱሪዝም ተቋማት ይገልጻሉ።
በተያዘው የፈረንጆች አመት ወደ ኢትዮጵያ ሊደረጉ የነበሩ የጉብኝት ፕሮግራሞች ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸውን የሳጋ አስጎብኚ ድርጅት ለጋዜጠው አስረድቷል።
አለም አቀፍ አስጎኚ ድርጅቶቹ ፕሮግራማቸው መቼ ቀጣይ እንደሚሆን ያሳወቁት ነገር የሌለ ሲሆን፣ በተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የሚገኙ ተመሳሳይ አስጎብኚ ተቋማትም ፕሮግራሞቻቸውን እየሰረዙ እንደሆነ ተነግሯል።
በአዲስ አበባ እንዲሁም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚገኙ በርካታ ሆቴሎች በቱሪስቶች ቁጥር መቀነስ ምክንያት ገቢያቸው እየቀነሰ መምጣቱን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን በቀጣዮቹ አምስት አመታት ሃገሪቱ ከአፍሪካ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዷ ለማድረግ አዲስ እቅድ መንደፉን በቅርቡ ይፋ አድርጓል።