ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2009)
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለእስር መዳረጉና እስራቱ አሁንም ድረስ መቀጠሉ ስጋት አሳድሮብኛል ሲል ማክሰኞ ገለጸ። ሃሳቡን የመግለጽ መብት እንዲከበር ህብረቱ አሳስቧል።
ህብረቱ በሃገሪቱ ባሉ የሰብዓዊ መብት አያያዞችና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር በአውሮፓ ህብረት ልዩ የሰብዓዊ መብቶች መልዕክተኛ በሆኑ ስታርቮስ ላምብሪኒደስ የተመራ የልዑካን ቡድን ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የሶስት ቀን ጉብኘት ማካሄዱን አስታውቋል።
ከመንግስት ጋር የተካሄደውን ውይይት ሪፖርትን ያወጣው የአውሮፓ ህብረት ከወራት በፊት ተግባራዊ ከተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለእስር በመዳረግ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
በሃገሪቱ ያሉ ህጎችና ደንቦች ዜጎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልፁ እንቅፋቶችን ፈጥሮ የሚገኝ በመሆኑ በህጎችና መመሪያዎች ላይ ማሻሻያዎች መደረግ እንዳለባቸው ህብረቱ አሳስቧል። የሰብዓዊ መብቶች ልዩ መልዕክተኛው ስታርቮስ ከሁለት አመት በፊት በሃገሪቱ የተካሄደው ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ባለመሆኑ ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈ የፖለቲካ ስርዓትና ሂደት ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል ሲሉ በሪፖርቱ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የፖለቲካ አመራሮችን ከእስር መልቀቅ፣ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት፣ እንዲሁም ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ተጥለው ያሉ ማነቆዎችን ማንሳት ለሚፈለገው አዲስ የፖለቲካ ስርዓትና አተገባበር አበይት ጉዳይ መሆናቸውን የአውሮፓ ህብረት አመልክቷል።
የአውሮፓ ፓርላማ በበኩሉ ባለፈው ወር ህብረቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ ዕርምጃን አልወሰደም በማለት ትችት ማቅረቡ ይታወሳል።
በተለይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በፓርላማ አባላቱ ከተጋበዙ በኋላ ወደ ሃገር ሲመለሱ ለእስር መዳረጋቸው አግባብ አለመሆኑን የአውሮፓ ፓርላማ ሲገልፅ ቆይቷል።
የአውሮፓ ህብረት ከህብረቱ ፓርላማ እንዲሁም ከተለያዩ አለም አቀፍ አካላት የቀረበለትን ቅሬታና አቤቱታ ተከትሎ አንድ የሰብዓዊ መብቶች ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ውሳኔ መድረሱ ታውቋል።
የዚሁ ልዑክ ሃላፊ የሆኑት ስታቭሮስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ምክክርን ያካሄዱ ሲሆን በተለይም የእስረኞች የመብት አያያዝ ጉዳይ መሻሻል እንዲደረግበት ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።
ከሶስት አመት በኋላ በሃገሪቱ ከሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ በፊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓቱ ከፍተኛ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባው የቡድኑ ሃላፊ አክለው አሳስበዋል።
የአውሮፓ ህብረት ከሁለት አመት በፊት በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ታዛቢ ቡድኑን ሳያሰማራ መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ የህብረቱ ሃላፊዎች ታዛቢ ቡድን መላኩ አስፈላጊ ሆኖ አለመገኘቱን ገልጸዋል።
ለበርካታ ሃገራትና አለም አቀፍ ስጋት ሆኖ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማሻሻያዎች ተደርጎበት እስከ ነሃሴ ወር ድረስ ቀጣይ እንዲሆን መወሰኑም የሚታወስ ነው።