ኢሳት (ታህሳስ 14 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጨማሪ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ መሆኑንና አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች ለእስር በመዳረግ ላይ እንደሚገኙ ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ።
መንግስት በህዝባዊ ተቃውሞ ተሳትፈዋል ተብለው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከ20 ሺ በላይ ሰዎች መካከል ወደ 10 ሺ የሚጠጉትን መልቀቁ ጥሩ ዜና ቢሆንም፣ ለአዋጁ መውጣት ምክንያት የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች ግን ምላሽ አለማግኘታቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል።
ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ያለምንም ክስ ለወራት ያህል በእስር ቤት መቆየታቸውን ያወሳው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲያበቃና የሃገሪቱ ዜጎች ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ጥሪውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በመልቀቅ ላይ ነኝ የሚላቸውን ሰዎች ከጅምሩም ቢሆን መታሰር አልነበረባቸውም ሲል በመግለጫው ያሰፈረው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጁቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ስቃዮች የተፈጸመባቸው ሰዎች ማነጋገር እንደተቻለም አመልክቷል።
ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል በኋላም በአማራ ክልል ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል።
የአዋጁ ተግባራዊነትን የሚከታተለውንንና የሚያስፈፅመው ኮማንድ ፖስት የአዋጁ መውጣትን ምክንያት በማድረግ ከ24ሺ በላይ ሰዎች በሁለት ዙሮች ለእስር መዳረጋቸውን ይገልጻል። ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለእስር የተዳረጉት ሰዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
ኢፍቱ የሚል ስም የተሰጣት አንዲት የ16 አመት ታዳጊ ወጣት በምትኖርበት ሃረርጌ ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አባቷን እንደገደሉባትና ሁለት ወንድሞቿ ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ከተወሰዱ በኋላ እስካሁን ድረስ ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ ለሂውማን ራይትስ ዎች አስረድታለች። ለደህንነቷ ሲባል ዋና ስሟ ያልተገለጸው ወጣቱ የቤት ለቤት ፍተሻ በተካሄደ ጊዜ እናቷ እና ሌላ ሁለት ወንድሞቿ መጥፋታቸውንም ተናግራለች።
ተመሳሳይ የስቃይ ሰለባ ነዋሪዎችን ማነጋገር እንደተቻለ ያስታወቀው ሂውማን ራይትስ ዎች ዶ/ር መረራ ጉዲና አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የዚሁ ሰለባ መሆናቸውን አክሎ አስፍሯል።
መንግስት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ አማራጭ የመፍትሄ መንገዶችን ሁሉ የዘጋ ድርጊት እንደሆነም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል።