የካቲት ፳፬ ( ሃያ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች የገጠመውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም የሚኒስትሮች ም/ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ያወጣው የአስቸኳዋ ጊዜ አዋጅ የተቀመጠለትን የስድስት ወራት ጊዜ ሊጨርስ አራት ቀናት ብቻ ቢቀሩትም፣ አዋጁን ለማንሳት ፍንጭ አለመታየቱ አዋጁ ሊራዘም ይችላል የሚለውን ግምት እያጠናከረው መጥቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ሀገሪትዋ በወታደራዊ አገዛዝ ስር ከወደቀች ጀምሮ ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች ባለፉት ስድስት ወራት ለሞት፣ ለእስር፣ ለድብደባ እና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች ታስረዋል። በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም ከየከተሞች እየታፈሱ ታሰረዋል። ህዝቡ ኢሳትና ኦኤም ኤንን እንዳይመለከት ለማድረግ ዲሹን እንዲነቅል፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ለውጭ ሚዲያዎች ምንም አይነት መግለጫ እንዳይሰጡ ተድርጓል። በሁዋላ ላይ በደረሰበት አለማቀፍ ተጽዕኖ ቢያነሳውም ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ ዲፕሎማቶች ከዋና ከተማዋ 40 ኪሜ ርቀው እንዳይሄዱ እገዳ ጥሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ በሁዋላ በአደባባይ የሚደረጉ ተቃውሞዎች፣ ከአደባባይ ወደ ህብዕ ተቃውሞ ተለውጠዋል። በርካታ ወጣቶች አገዛዙን በትጥቅ ትግል ለማንበርከክ ጫካ ገብተዋል። የቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፣ በርካታ አለማቀፍ ኮንፈረንሶችም ተሰርዘዋል። የውጭ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀንስ፣ በርካታ ድርጅቶችም ስራ አቁመው አገሪቱን ጥለው ወጥተዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ እንደኢንተርኔት ያሉ አገልግሎቶች መቋረጥና መስተጓጎል ሀገሪቱ ከዘርፉ ታገኝ የነበረውን ከፍተኛ ገቢ ያስቀረ ሲሆን፣ በተጨማሪም በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክያንያት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች በስተቀር ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ አግኝተው ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአደባባይ ይደረግ የነበረውን ተቃውሞ በተወሰነ ደረጃ መቀነሱ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም፣ በህቡዕ የሚደረገውን ትግል አላስቆመውም። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አሁንም የመሳሪያ ትግል በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ በአቤንሻንጉል ጉምዝና በኦሮምያና በሶማሊ ክልል ድንበሮች አሁንም ግጭቶች አሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ፍንጭ አለመኖሩን የገለጸው ዘጋቢያችን፣ አዋጁ እስከ ፊታችን ማክሰኞ የማይነሳ ከሆነ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መንኮታኮት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል የተለያዩ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ዘግቧል።
በሌላ በኩል ለአዋጁ ስኬት እንደ ማሳያ ተደርጎ በህወሃት/ኢህአዴግ በኩል የሚቆጠረው በአገር ውስጥ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚደረገው ውይይት ሲሆን፣ ውይይቱ በእስካሁኑ ፣ ቀጣዩ ሂደት ድርድር ይሁን ወይስ ክርክር በሚለው ላይ ሰማያዊ ፓርቲን የወከሉት አቶ የሽዋስ አሰፋና መድረክን የወከሉት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ከገዢው ፓርቲና ደጋፊዎቹ ጋር ክርክር አድርገው፣ በልዩነት ተለያይተዋል።