ጥቅምት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንም አይነት የስራ ማቆም አድማ ማድረግም ሆነ መሰብሰብ ህገወጥ መሆኑን ዝርዝር መመሪያ ካወጣ የሞጣ ከተማ መምህራን የስራ ማቆም አድማ በማድረግ የመጀመሪያ ሆነዋል።
መምህራኑና ተማሪዎች ትናንት የጀመሩትን ተቃውሞ ዛሬ ትምህርት በመዝጋት የቀጠሉ ሲሆን፣ የከተማዋ ባለስልጣናትና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ተማሪዎችን እና መምህራንን በማስፈራራት ትምህርት እንዲጀምሩ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። መምህራኑና ተማሪዎች አድማውን ያደረጉት መምህር ሰለሞን አንዳርጌ መታሰራቸውን ተከትሎ ነው። መምህር ሰለሞን በአካባቢው የሚደረገውን ታቃውሞ ያስተባብራል በሚል በኮማንድ ፖስቱ አባላት መታሰራቸውን የአካባቢውም ምንጮች ገልጸዋል። የከተማው ፖሊስ መምህሩ ስለሚገኝበት ቦታ እንደማያውቅ ለመምህራኑ ተናግሯል። ትናንት ምሽትና ሌሊት ሞጣ ከተማ በውጥረት ማሳለፉዋን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በፍኖተሰላም 70 ወጣቶች ባለፉት ሁለት ቀናት ተይዘው ታስረዋል። ወጣቶቹ በአካባቢው ተደርጎ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ አስተባብራችሁዋል በሚል ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል። በወገራ ወረዳ አምባ ጊዮርጊስ ከተማ ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ የመከላከያ አባላት 47 ወጣቶችን አፍሰው ሲወስዱ፣ ፖሊሶች ደግሞ 27 ወጣቶችን ይዞ ማሰሩን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።