የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአጭር ጊዜ ውስጥ መነሳት አለበት ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 30/2010) በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአጭር ጊዜ ውስጥ መነሳት እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴሊርሰን አሳሰቡ።

ኢትዮጵያን ጎብኝተው ወደ ጅቡቲ ያመሩት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ያለው ችግር ሊፈታ የሚችለው ነጻነትን በማስፋት ብቻ ነው ብለዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቴሊርሰን አምስት የአፍሪካ ሃገራትን ለመጎብኘት በጀመሩት ጉዞ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ጉብኝት አድርገው ጅቡቲ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴሊርሰን ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ የሰጡት መግለጫ ደግሞ የተደበላለቀ ስሜትን የሚያጭር መሆኑ ነው የተገለጸው።

በአንድ በኩል በሰጡት መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲነሳ የጠየቁበት ሁኔታ ነበር።

ይህን ሲሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይልቅ ነጻነትን ማስፋት ትክክለኛ መፍትሄ መሆኑን ነው ያሳሰቡት።

እናም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥሰትን ሊያስከትል እንደሚችል ሬክስ ቴሊርሰን ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በፈቃዳቸው ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸው የዲሞክራሲ ሂደትን ያፋጥናል፣ተተኪ ሰው መምረጥም የስልጣን ሽግግርን ያመጣል ማለታቸው በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ያለ እንዲመስል የሚያደርግ ነው ሲሉ ትችታቸውን የሰነዘሩባቸው በርካቶች ናቸው።

እናም አሜሪካ አሁን ያለው አገዛዝ እንዲቆይ የፈለገች ይመስላል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቴሊርሰን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁም ቻይና በአፍሪካ ሃገራት ኢንቨስትመንትን የምታስፋፋው የአፍሪካ ሃገራትን በብድር በመዝፈቅ መሆኑ ጉዳቱ ሊያምዝን እንደሚችል መምከራቸው ነው የተነገረው።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴሊርሰን ከኢትዮጵያ ጅቡቲ ከዚያም በኬንያና በቻድ እንዲሁም በናይጄሪያ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ወደ ሃገራቸው እንደሚመለሱ ይጠበቃል።።