የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ ቤት የማፍረሱ ዘመቻ ተጀመረ

ጥቅምት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች ቤት የማፍረሱ እንቅስቃሴ እንደአዲስ ተጀምሯል። በለገጣፎና አካባቢዋ ዛሬ በርካታ ቤቶች የፈረሱ ሲሆን፣ ብዛት ያላቸው የፌደራል ፖሊስ አባላትና ቀይ ኮፍያ ለባሽ የአጋዚ ወታደሮች በብዛት ቁጥጥር ሲያደርጉ ውለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዜጎች አገዛዙ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ማንኛውንም አይነት ተቃውሞ ማድረግ ስለማይችሉ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ቤት የማፍረሱ ዘመቻ ተጠንከሮ እንዲቀጥል ፍላጎት መኖሩን ዘጋቢያችን ገልጿል። ቤቶቻቸው የሚፈርሱባቸው ሰዎች ፣ ተቃውሞ ባለማሰማት በአካባቢው ራቅ ብለው የፕላስቲክ መከለያዎችን እየዘረጉ እየተጠለሉ ነው።

የኢህአዴግ አገዛዝ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ልዩ ዞኖች ቤት የማፍረስ እንቅስቃሴ መቆሙን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ባለፉት ሁለት አመታት በተደረገው ቤት የማፍረስ ዘመቻ ከ100 ሺ በላይ ዜጎች ቤት አልባ ሆነዋል።