ጥቅምት ፲፭ (አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያና በአማራ አካባቢዎች የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ወጣቶችን በገፍ የማሰር እንቅስቃሴው በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሎአል። የእስሩ ዘመቻ ወደ ደቡብ፣ ሀረር ፣ ድሬዳዋና ጋምቤላ ሳይቀር የተዛመተ ሲሆን፣ የኮማንድ ፖስት አባላት ነን የሚሉ መለዮ የለበሱና ያልለበሱ ሰዎች ወጣቶች እያስቆሙ ፈትሸው ሞባይላቸውንና ገንዘባቸውን ከቀሙ በሁዋላ፣ ንብረታቸውን ሲጠይቁ ፣ እስር ቤት መግባት ትፈልጋለህ ወይም ዝም ብለህ ትሄዳለህ እንደሚባሉ ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል። ሴቶች ቦርሳቸው እየተፈተሸ ገንዘብ ካላቸው ገንዘባቸው ይወሰድባቸዋል።
የአካባቢው ካድሬዎች በቂም በቀል በመነሳሳት በርካታ ወጣቶች እንዲያዙ እያደረጉ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎች ወጣቶች ለአወደማችሁት ንብረት ካሳ ክፈሉና ትወጣላችሁ እየተባሉ ነው። ከፍተኛ አፈና እየተፈጸመባቸው መሆኑን የሚናገሩት ወጣቶች ሁኔታው ከሚችሉት በላይ ሆኖባቸዋል።
በኦሮምያ በጉጂና ቦረና ዞኖች አሁንም ድረስ ጫካ ውስጥ የሚያድሩ ሰዎች በብዛት አሉ። “አገዛዙ ወጣት የሚባል ነገር ማየት አይፈልግም” የሚሉት ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ሰዎች፣ በየወረዳው ያሉ ካድሬዎች በህዝባዊ ተቃውሞው ወቅት የደረሰባቸውን ጉዳት ለመበቀል ፣ አስከፊ እርምጃ እየወሰዱ ነው ይላሉ።
በሌላ በኩል መሳሪያ የመግፈፍ እንቅስቃሴው እንዳለ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የአካባቢ ሚሊሺዎች፣ ህዝቡን ደፍረን መሳሪያህን አስረክብ ለማለት አንችልም በማለት፣ መሳሪያ በመቀማቱ ስራ ላይ ተሳታፊ እንደማይሆኑ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ በአማራ ክልል በስፋት ይጀመራል የተባለው መሳሪያ የመቀማቱ እንቅስቃሴ ፍጥነቱን የቀነሰ ቢመስልም፣ ገዢው ፓርቲ አርሶአደሩን አዘናግቶ መሳሪያውን ለመቀማት በማሰቡ ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያድርግ በክልሉ የሚገኙ የትግሉ አስተባባሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
በመላው አገሪቱ የሞባይል ኢንተርኔት እንዲቋረጥ መደረጉን ተከትሎ ወጣቶች መረጃዎችን በየጊዜው ለመከታተል አልቻሉም።