መጋቢት ፳ (ሃያ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ያለምንም ማስረጃ በሽብር ወንጀል ተከሰው በቃሊቲ ማጎሪያ ቤት የሚገኙት፥ አስቴር ስዩም እና ንግስት ይርጋ፥ ትናንት መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም በልደታ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም አሁንም ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል።
አስቴር ስዩም እና ንግስት ይርጋ የቀረቡት አቶ ሄኖክ ከተባሉ የሕግ ጠበቃ ጋር ሲሆን፥ በንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ አጠቃላይ የቀረቡት ስድስት ተከሳሾች ናቸው።
እነሱም የአማራ ማንነት ጥያቄ የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ወጣት ንግሥት ይርጋ፣ የሰሜን ጎንደር የማክሠኝት መኢአድ አስተባባሪ አቶ ዓለምነህ ዋሴ ፣ የሰሜን ጎንደር መኢአድ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ያሬድ ግርማ፣ የወልቃይት ጠገዴ ተወካይ አቶ ጌታቸው እና አቶ ቴዎድሮስ ተላይቁሜ እና አቶ አወቀ አባተ ናቸው።
አስቴር ስዩምን በተመለከተ፥ አቃቤ ሕግ ያቀርባል የተባለው ሪከርድ የተደረገ የስልክ መረጃ በአሁኑም ችሎት ስላልቀረበ ዳኞቹ የተለመደውን የጊዜ ቀጠሮ ሊያሰሙ ሲሉ፥ ተከሳሽ አስቴር ስዩም ከዚህ በፊት በቀጠሮ ለብዙ ጊዜ መጉላላቷን በመግለጽ ፍትህ እንደዘገየባትና በፍርድ አሰጣጥ ላይ ያላትን ቅሬታ የተለያዩ የፍትህ አንቀፆችን በማጣቀስ ተናግራለች።
“እኔ ጥፋተኛ አይደለሁም፥ ምንም አይነት መረጃ በሌለበት ሁኔታ በነጻ መለቀቅ ሲገባኝ ለብዙ ጊዜ በእስር ቤት እየተሰቃየሁ እገኛለ” ያለችው አስቴር፥ የሚቀጥለው ቀጠሮ የመጨረሻ እንዲሆንላት ችሎቱን ተማፅናለች።
ዳኞችም እርስ በእርሳቸው ከመከሩ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ “ተቀርጿል የተባለውን መረጃ ልዩ ትዕዛዝ ሰጥተን እናስቀርባለን “በማለት ለመጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ በመስጠት የእለቱን ችሎት ጨርሰዋል።
ትናንት መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛ ፍርድቤት የዋለውን ችሎት በዳኝነት ተሰይመው ያስቻሉት ዳኞች፥ ዳኛ በላይነህ አወል ፣ ዳኛ ያዕቆብ መኩሪያው እና ዳኛ ግርማ ናቸው።