የአሰሪና ሰራተኛ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የሰራተኞችን መብት ያፍናል ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 17/2010)የአሰሪና ሰራተኛ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የሰራተኞችን መብት እንደሚያፍን ተገለጸ።

አዋጁ የመንግስት ሰራተኞችን የመደራጀት መብት የሚከለክልም ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን በጽህፈት ቤቱ ጥቅምት 13 2010 በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰጠውን የተቃውሞ መግለጫና የቀጣይ ርምጃዎች ማስጠንቀቂያን ተከትሎ ሰራተኞች እስከ ስራ ማቆም አድማ የሚሄድ ዝግጁነት እያደረጉ መሆኑን የተለያዩ ፋብሪካዎች የሰራተኛ ማህበራት አመራሮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉና የሰራተኛ ማህበራቱ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላይ ምክር ቤት አባላት እንደገለጹት ረቂቅ ሕጉ ያካተታቸው አንቀጾች ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች ይጻረራል።

ፓርላማው የሚተዳደርበትን የኢህአዴግ ህገ መንግስት ይጥሳል።

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 27 ላይ ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውል የሚቋረጥበት ሁኔታ መካተቱ ለሰራተኞች ስጋት ከመፍጠሩም በላይ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነት ያህል ሰራተኞች በወር ውስጥ ከሁለት ቀን በላይ ማርፈድ እንደማይችሉ በረቂቅ ሕጉ መካተቱ በሀገሪቱ የተመቻቸ የትራንስፖርት አገልግሎት በሌለበት ስርአት ውስጥ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በተለይ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ ከተሞች ያለው የትራፊክ መጨናነቅ በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ በረቂቅ ሕጉ በስድስት ወር ውስጥ ለአምስት ጊዜ የስራ ሰአት አለማክበር በአሰሪው በኩል ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውል ለማቋረጥ እንደሚያበቃ መደንገጉ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡት የኮንፌዴሬሽኑ ጠቅላይ ምክር ቤት አባል ረቂቅ አዋጁ የመንግስት ሰራተኞችን የማይመልከት ሆኖ መቅረቡ እጅግ እንዳስደነገጣቸውና የመንግስት ሰራተኛውን የመደራጀት መብት የጣሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረቂቅ አዋጅም ሆነ በመንግስት ሰራተኞች አስተዳደር አዋጅ ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች እንዲደራጁ አለመፈቀዱ ሰራተኛው የመብት ጥያቄ በተደራጀ መንገድ እንዳያነሳ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

የመንግስት ሰራተኛው የተጋረጠበትን አደጋ ተገንዝቦ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ጥሪ አቅርበዋል።