መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የታዋቂዋ አርቲስት የቀብር ስነስርዓት በ ቅድስ ስላሴ ካቴደራል ወዳጅ ዘመዶቿና አድናቂዎቿ በተገኙበት ተፈጽሟል።
አርቲስት ሰብለ ተፈራ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ወሎ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አይቤክስ ሆቴል አካባቢ በግንቦት ወር 1968 ዓም. የተወለደች ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በንፋስ ስልክ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቃለች። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም በዛው የንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጨርሳለች። ሕይወቷ እስካለፈበት ቀን ድረስ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቲያትሪካል አርት ትምህርት ክፍል የዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች እንደ ነበር ግለ ታሪኳ ያስረዳል።
ተዋናይ ሰብለ ተፈራ ከ20 በላይ ፊልሞች እንዲሁም ከ30 በላይ በሚሆኑ ቲያትሮች ላይ በመተወን ከመድረክ ፈርጦች መካከል አንዷ ስትሆን፣ ከተወነቻቸው መካከል ጓደኛሞች ፣ላጤ፣ ሰቀቀን ፣ የሰርጉ ዋዜማ፣ ህይወት በየፈርጁ ፣እቡይ ደቀመዝሙር ፣ አምታታው በከተማ፣ የክፉ ቀን ደራሽ ፣አንድ ቃል፣ ወርቃማ ፍሬ፣ እንቁላሉ፣ 12 እብዶች በከተማ፣ ሩብ ጉዳይ፣ አብሮ አደግ የተወሰኑት ናቸው። ተዋናይት ሰብለ ተፈራ በተወለደች በ39 ዓመቷ በአዲሱ ዓመት መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ባጋጠማት ድንገተኛ የመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። የዝግጅት ክፋላችን ለአርቲስቷ ቤተሰቦችና አድናቂዎቿ መጽናናትን ይመኛል።