ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2009)
የአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደር ዞን የተለያዩ ስፍራዎች ማክሰኞ ምሽት ጥቃት ፈጸሙ። ከአይን ምስክሮችና ከንቅናቄው ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለው በጭልጋ፣ ደንቢያና በጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች በተመሳሳይ ቀንና በተቀራራቢ ሰዓት በመንግስት ሃይሎችና ተቋማት ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።
በትግል ላይ እያሉ መስዋዕትነት በከፈሉት ሻለቃ መሳፍን ጥጋቡ ወይንም ገብርዬ እንዲሁም በታጋይ ጎቤ መልኬ እና በአበራ ጎባው ስም የተሰየሙት ወታደራዊ ዘመቻዎች፣ ማክሰኞ መጋቢት 5 ፥ 2009 የመከላከያ ሰራዊት አባላትን መግደልና መቁሰል ጭምር ማስከተላቸውንም ለመረዳት ተችሏል።
ዘመቻ “ዋዋ” የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚሁ ጥቃት ከጎንደር 80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል። በጭልጋ ወረዳ ነጋዴ ባህር ከተማ በሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በተሰነዘረ ድንገተኛ ጥቃት 3 ወታደሮች ሲገደሉ፣ 15 መቁሰላቸው ተመልክቷል። በአምስቱ ላይ የደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ጎንደር ሬፈራል ሆስፒታል ሲወስዱ፣ ቀላል ጉዳት የደርሰባቸው 7 ወታደሮች በመተማ ገንዳ ውሃ ሆስፒታል በህክምና ላይ መሆናቸውን የተገኘው ዜና ያስረዳል።
በቅርቡ በትግል ሜዳ ላይ እያሉ የተሰውትን ጎቤ መልኬን ለማስታወስም በስማቸው መጠሪያ “ዋዋ” የተሰየመው ዘመቻ ተሳታፊ የሆኑት የአርበኞች ግንቦት 7 ተዋጊዎች ጥቃቱን ፈጽመው ወደ ነበሩበት መመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በመከላከያ ሰራዊት በኩል በቡድን መሳሪያ የተደገፈ የአጻፋ ምላሽ መሰጠቱም ተመልክቷል። በመትረየና ላውንቸር የተደገፈውን የአጸፋ ምላሽ ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መንገሱንና የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡም ተመልክቷል።
በዚሁ በጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ በተመሳሳይ ቀን ዘመቻ ገብርዬ በሚል በተሰየመው ወታደራዊ ዘመቻ በቆላ ድባ ከተማ በሚገኝ የከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት ላይ በተከፈተ ዘመቻ የአስተዳደር ጽ/ቤቱ በከፊል ሲወድም፣ የአስተዳዳሪው መኪና መቃጠሉንም የመጣው ዜና ያስረዳል። በተመሳሳይ ጯሂት ከተማ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በካምፕነት በሚጠቀሙበት ቁጥር 2 በተባለው ጽ/ቤት ላይ በተሰነዘረ ጥቃት በወታደሮቹ ላይ የቃጠሎ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በአብራጅራ ከተማ አብራጅ ጽ/ቤት በሰፈሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ እንዲሁም በቸንከር ቀበሌ የከተማዋ ኮማንድ ፖስት ማዘዣ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። በጥቃቱ የቸንከር ቀበሌ ኮማንድ ፖስት ማዘዣ ጣቢያ ሲወድም፣ አንድ የኮማንድ ፖስቱ አባል መጎዳቱንና አንድ መጋዘን መቃጠሉን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች መሳሪያ አንስተው በትግል ላይ ከነበሩት አንዱ በነበረውና መስዋዕትነት በከፈለው በአበራ ጎባው ስም በተመሳሳይ ቀን በጎንደር ዙሪያ የአርበኞች ግንቦት 7 ሃይሎች ጥቃት መፈጸማቸውም ተመልክቷል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ተዋጊዎች ማክሰኞ መጋቢት 5 ፥ 2009 እኩለ ሌሊት አካባቢ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በደጋማ ከተማ በወህኒ ቤት እንዲሁም ኮማንድ ፖስቱ በሚጠቀምባቸው ቢሮዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል። እንዲሁም የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል በሆኑት በአቶ ደሴ ዘገየ መኖሪያ ቤት ላይም ተመሳሳይ ጥቃት መከተሉንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።