(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 5/2010) የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዲሞክራሲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ ለሐገሪቱ መረጋጋትና የተቋማት ግንባታ እንጂ ለምርጫ አይደለም ሲሉ ተናገሩ።
የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይህንን የገለጹት ከ10 አመታት ስደትና ትግል በኋላ ትላንት ወደ ሃገራቸው በገቡበት ወቅት ነው።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ደማቅ የአቀባበል ስነስርአት ላይ ከዋና ጸሐፊው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ከሌሎች የአመራሩ አባላት ጋር የተገናኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ወደ ሀገራችን የገባነው ሃገሪቱ ተረጋግታለች በሚል አይደለም ብለዋል።
ነገር ግን በማረጋጋቱ ሒደት የራሳችንን አስተዋጽኦ ልናደርግና የሚጠይቀውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ጭምር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የተገኘው ለውጥ እንዲመጣ በሩቅም ሆነ በቅርብ ሆነው መስዋዕትነት ለከፈሉ እንዲሁም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሒደቱን በማፋጠን ሐገሪቱን ከአደጋ ለታደጉት የለውጥ ሃይሎች የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዲሞክራሲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ምስጋና አቅርበዋል።
ሊቀመንበሩ ወደ ሃገራችን በመመለሳችን የምናወራርደው ቂም አይኖረንም ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ሁሉንም ጥያቄ በአንዴ ሊመልስ ስለማይችል ሁሉንም በአንዴ እንዲመለስ መጠየቅ ደግሞ የለውጥ ሃይሉን ሊከፋፍለውና ለለውጥ አደናቃፊው እድል ሊሰጥ ስለሚችል የጥንቃቄ ጉዞ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ስልጣናቸውን ያጡት ወገኖች ካልበላሁት ጭሬ ልበትነው የሚለውን የእንስሳዋን መንገድ ከተከተሉ ለእነርሱም ጭምር የማይጠቅም እንደሆነና ከእንግዲህ ያን ዘመን መልሶ ማምጣት እንደማይቻል ገልጸዋል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በበኩላቸው ትግሉ ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም ብለዋል።
ዜጎች በሃገራቸው ሰርተው፣ተመችቷቸው መኖር እስኪችሉ ድረስ ለሃገራቸው የሚደረገው ትግል እንደሚቀጥል በአጭር መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ነአምን ዘለቀ፣አቶ ኤፍሬም ማዴቦና ሌሎች አመራሮች ኣንዲሁም ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የተጓዙ የድርጅቱ አባላት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ስነስርአት ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የአቀባበል ስነስርአት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኢትዮጵያ ሐገራችን ስትሉ፣ ለሕይወታችሁ ሳትሳሱ በትግል ቆይታችሁ እንኳን ወደ ሃገራችሁ ተመለሳችሁ ያሉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራው የለውጥ ሃይል በውስጥ ያደረገውን የሞት ሽረት የለውጥ ግብግብም በአጽንኦት አንስተዋል።