የአምቦ ዩንቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት አይታይም ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤት በደብዳቤ አሳወቀ

የአምቦ ዩንቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት አይታይም ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤት በደብዳቤ አሳወቀ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ/ም) ከሶስት ሳምንት በፊት የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ከሕግ አግባብ ውጪ በኮማንድ ፖስቱ ተይዞ ማእከላዊ እስር ቤት የሚገኘው በአምቦ ዩንቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረበም። ፍርድ ቤቱ የካቲት 30 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት ለመጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም የ14 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ቢሰጠውም ፖሊስ ሊያቀርበው ፈቃደኛ አልሆነም።
ጦማሪ ስዩም ክስ ያልተመሰረተበት፣ ዋስትናም ያልተሰጠው ወይንም ክሱ ያልተቋረጠ በመሆኑ ፖሊስ ሊያቀርበው ይገባ ነበር። ፍርድ ቤቱ ፌደራል ፖሊስ ያላቀረበበትን ምክንያት እንዲገልፅ፣ ተጠርጣሪውንም እንዲያቀርብ ለመጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። በእለቱ ጦማሪ ስዩም ተሾመ ፍርድ ቤት ያልቀረበ ሲሆን
ጉዳዩ ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጭ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚቋቋም ፍርድ ቤት እንደሚታይ ፖሊስ ለፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በደብዳቤ አሳውቋል።
ፍርድ ቤቱም በፌደራል ፖሊስ ጥያቄ መሰረት የጦማሪ ስዩም ተሾመን የጊዜያዊ ቀጠሮ መዝገብ እንዲዘጋ ወስኗል። ጦማሪ ስዩም ተሾመ ከዚህ ቀደም በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለሦስት ወራት ታስሮ መፈታቱ ይታወሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ህዝብ በተገኘበት ችሎት የዋልድባ መነኮሳት የአንድ ወር ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጣቸው።
ታሪካዊው የዋልድባ ገዳም ይዞታችን አይነካ ማለታቸውን ተክትሎ በእስር ቤት ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት ላይ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማሰማት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች አቅርቦ ምስክርነታቸውን እንዲያሰማ ለመጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም በሰጠው ቀጠሮ ችሎት ላይ የተገኙት የዋልድባ መነኮሳት አባ ገብረየሱስ ኪዳነማርያም እና አባ ገብረስላሴ ወልደሃይማኖትን ጨምሮ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ አብረዋቸው የተከሰሱት አቶ ነጋ ዘላለም ፍርድ ቤት ተገኝተዋል።
ከሳሽ አቃቤ ሕግ ምስክሮቹ በምን ምክንያት እንደቀሩበት በችሎቱ ተጠይቆ የማእከላዊ መርማሪ የሆኑት አቶ አብዲ “ምንም የማውቀው ጉዳይ የለም” ሲሉ ምላሽ በመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።፡
የተከሳሽ ጠበቆችም የአቃቤ ሕግ ምስክሮች በተደጋጋሚ መቅረታቸውን በመግለፅ አቃቤ ሕግ ማስረጃቸውን በጊዜው የማቅረብ ግዴታ ያለባቸው ቢሆንም ሳያቀርብ ቀርቷል። ይህ ደግም ፍትህን የሚያጓድልና የፍርድ ቤቱንም የሥራ ሂደት እንደሚያጓድል አስረድተው ከፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክር የማቅረቡ ሂደት ታልፎ ለብይን እንዲቀጠርላቸው በአፅንኦት አስረድተዋል።
ፍርድ ቤቱ አቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ ምስክሮች የቀሩበትን ምክንያት ባልገለፁበትና ምንም እንደማያውቁ በተናገሩበት ሁኔታ ተጨማሪ ጊዜ ሊሠጥ ይገባል በማለት ለሚያዚያ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት በአራተኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾች ወደ ችሎት በሚገቡበት ጊዜ ሁሉም ታዳሚ ከመቀመጫው በመነሳት ለደቂቃዎች በመቆም አክብሮቱን ገልፆላቸዋል። ታዳሚው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም በችሎት ድምፅ አሰምቷል። በዚሁ መዝገብ ከተካተቱ 35 ተከሳሾሽ መሃከል 32ቱ ክሳቸው ተቋርጦ አሁን ያሉት 3 ተከሳሾች ብቻ መቅረታቸውን ጦማሪ ሙጂብ አሚኖ ዘግቧል።