የአምባጊዮርጊስ ከተማ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

ነሃሴ  ፲፪ ( አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ አምባጊዮርጊስ ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች ዛሬ ነሃሴ 12፣ 2008 ዓም ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ አርፍደዋል። በከተማዋም ሆነ በአካባቢው ምንም አይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ያልነበረ ሲሆን፣ በአካባቢው የተሰማሩ ፖሊሶችም አንዳንድ ወጣቶችን ከመደብደባቸው በስተቀር ምንም እርምጃ አልወሰዱም።

ህዝቡ “ወያኔ አይገዛንም፣ 25 አመታት የተቀለደብን ይበቃል፣ በቃን!” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች በማሰማት ተቃውሞውን ሲገልጽ መዋሉን በስፍራው የተገኙ ወጣቶች ለኢሳት ገልጸዋል ።

በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች  ለ3 ቀናት የሚቆይ የስራ ማቆም አድማ ካደረጉ በሁዋላ፣ በአጋዚ ወታደሮች የተገደሉ ሰማአታትን ለመዘከር  የሻማ ማብራት ስነስርዓት ማድረጋቸውን ተከትሎ አንዳንድ ወጣቶችን ለማሰር እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ወጣቶቹ የሻማ ማብራት ስነስርኣቱን ለማድረግ እንደማይችሉ በታጣቂዎች ቢከለከሉም፣ ማስፈራሪያውን ወደ ጎን በማለት እቅዳቸውን አሳክተዋል።

በደብረታቦር ከተማም ደግሞ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ለምን ተዘዋውራችሁ በፍጥነት አትጭኑም በሚል ሾፌሮች በግል እየተጠሩ ሲደበደቡ የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃ ደርሶናል። የባህርዳርን እና የጎንደሩን የተቃዉሞ ሰልፍ ደግፋችሁዋል የተባሉ 9 ሰዎች ነሃሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም በመንግስት ታጣቂዎች ተይዘዉ መታሰራቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።