ሚያዝያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ምክትል የውጭ ጉዳይ ሃላፊዋ ውንዲ ሸርማን በቅርቡ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በመንግስት ሚዲያ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲና ምርጫ አድንቀው መናገራቸው ከየአቅጣጫው ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል። ዋሽንግተን ፖስት የተባለው ታዋቂ ጋዜጣ በርእሰ አንቀጹ ወንዲ ሽርማንን የተቸ ሲሆን፣ ባለስልጣኗም ጋዜጣው በተሳሳተ መንገድ እንደተረዳቸውና ትችቱ ተገቢ አለመሆኑን በጽሁፍ መልስ ሰጥተዋል።
ባለስልጣኗ ኢትዮጵያ አስቸጋሪ በሆነበት አካባቢ አልሸባብን በመዋጋት፣ በደቡብ ሱዳን ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ትልቅ አጋር መሆኑዋን ገልጸው፣ በአለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን ለማሳከት ትልቅ እድገት ማስመዝገቡዋን ገልጸዋል።
መረጋጋት፣ ደህንነትና የኢኮኖሚ ልማት ዘላቂነት ሊኖራቸው የሚችለው የዲሞክራሲ እሴቶች ሲከበሩ ብቻ ነው የሚሉት ባለስልጣኑዋ፣ ኢትዮጵያ ሙሉ ዲሞክራሲ ለማስፈን ረጅም መንገድ እንደሚቀራት በአደባባይ ገልጫለሁ ብለዋል።
በጉዞየ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲን በተመለከተ ገና ታዳጊ አገር መሆኑዋን፣ በጊዜ ሂደት የፖለቲካ ስርአቱ እየተጠናከረ እንደሚሄድና ህዝቡ እውነተኛ አማራጭ የሚያገኝበት ሁኔታ እንደሚፈጠርለት ተስፋ እንደምናደርግ ገልጫለሁ ብለዋል ባለስልጣኗ።
ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በላይ ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞች ማሰሩዋን የገለጹት ዌንዲ ሸርማን፣ አሜሪካ ዲሞክራሲንና ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ በግልጽ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግራለች ሲሉ አክለዋል። የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን፣ የነጻ ጋዜጠኞች እስርና አያያዝ እንዲሁም የጸረ ሽብር ህጉ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥቂያ እየዋለ መሆኑን እና ሁኔታውም አሳሳቢ መሆኑን ለባለስልጣናቱ ገልጫለሁ ያሉት ሸርማን፣ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ በቅርብ እንደሚከታተለው እንዲሁም በአገሪቱ ዲሞክራሲ እንዲያብብ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርብ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።