ሐምሌ ፩( አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ( ሴናተሮች) የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የሚፈጽመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አውግዘዋል።
የሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የኦባማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታ እንደገና እንዲመረመር የቀረበለትን ፕሮፓዛል ደግፎ ሙሉ ቤቱ እንዲወስንበት ውሳኔውን አስተላልፏል።
ውሳኔው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ነው። “ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበር እና አሳታፊ ስርዓት እንዲገነባ” የሚል ትርጉም ያለው የህግ ረቂቅ የመጀመሪያውን ሂደት ያለፈ ሲሆን፣ ሴኔቱ ወደ ስራ ሲገባ ሙሉ በሙሉ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ህጉ በርካታ ጥያቄዎችን የያዘ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንዲሁም አፋኝ የሆኑት ህጎች እንዲለወጡ ይጠይቃል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጆን ኬሪ ለኢትዮጵያ ለደህንነት በሚል የሚሰጠው እርዳታ እንደገና እንዲመረምሩ ረቂቅ ህጉ ይጠይቃል። የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት የሜሪላንድ ሴናተር ቤን ካርዲን ናቸው። የአቶ አንዳርጋቸውን ጽጌ የሚከታተሉት የሪፕሪም ዳይሬክተር ማያ ፎጋ የአሜሪካ ሴናተሮች የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች በተቃዋሚዎችና በጸሃፊዎች ላይ የሚፈጸመውን ተደጋጋሚ የመብት ጥሰትና አፈና ማውገዛቸው ትክክል ነው ይላሉ።
የኦባማ በመንግስት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲኖር የሚፈልግ ከሆነ ከኮንግረስ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመስማት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሁሉም የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በተያያዘ ዜናም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ እንግሊዝ በቅርብ እየተከታተለችው መሆኑን የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ጉዳዩን ማንሳታቸውን የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፣ ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ እየተነጋገርንበት ነው ብለዋል።